ለማእከሉ መቋቋም የመሰረት ድንጋይ ቢቀመጥለትም እስካሁን ግንባታው መጀመር አልተቻለም።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ኘሮፊሰር ንጉሴ ደቻሳ የምርምር ማእከሉን ግንባታ ጀምሮ መሰረተ ልማት ለማሟላት በጀት እንዳልተለቀቀለት ለጣቢያችን አስታዉቀዋል።
ተደጋጋሚ የካፒታል በጀት ጥያቄዎች ማቅረባቸዉን የገለፁት የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኘሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ መልስ እንዳላገኙ አንስተዋል።
በክልሎች ጥያቄ መሰረት የተቋቋሙ የምርምር ማዕከላት ችግሮች እንደታዩባቸዉ የግብርና ሚኒስቴር የ2017 ዓ.ም የ6 ወር ዕቅድ አፈጻፀም ሪፖርት ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት ይህ የምርምር ማእከል በምሳሌነት ተጠቅሷል።
ከኢትዩ ኤፌም ጋር ቆይታ ያደረጉት ዋና ዳይሬክተሩ ይህንን የበጀት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘት ከቻለ አስፈላጊ ነገሮችን በማሟላት ማእከሉን ወደ ስራ ለማስገባት እንችላለን ብለዋል።
አያይዘዉም ይህ ጥያቄ መልስ ያገኛል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ሲሉ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዮት የወረኢሉ የግብርና ማእከልን በወረኢሉ ከተማ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ በ2014 አ.ም አስቀምጧል።
በአገር አቀፍ ደረጃ በአሁኑ ወቅት 23 የምርምር ማእከላት በተለያዩ ክልሎች እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል።
ቁምነገር አየለ
ጥር 30 ቀን 2017 ዓ.ም
