በአገራችን ከ 1 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ከሚጥል ህመም ጋር የሚኖሩ ዜጎች መኖራቸዉንም ሰምተናል፡፡
10ኛዉ ብሄራዊ የሚጥል ህመም ቀን መከበር በጀመረበት ዕለት የተገኙት የጤና ሚኒስቴር ድኤታ ዶክተር ደረጄ ድጉማ፤ባለፈዉ ዓመት 2መቶ27ሺህ የሚሆኑ ከሚጥል ህመም ጋር የሚኖሩ ዜጎች ህክምና ማግኘታቸዉን ገልጸዋል፡፡
ህመሙ ካለባቸዉ ዜጎች ቁጥር አንጻር ሲታይ ትንሽ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትር ድኤታዉ፤ ህክምናዉን ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸዉን አንስተዋል፡፡
አሁን ላይ ለሚጥል ህመም አጋላጭ እየሆኑ ከመጡ ጉዳዮች መካከል የትራፊክ አደጋ አንዱ መሆኑን ገልጸዉ ፤ በዚህ ዙሪያ መሻሻል ያለባቸዉ ጉዳዮች መኖራቸዉን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ እንደ ስትሮክ እና ጭንቅላት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ለሚጥል ህመም መነሻ ምክንያቶች እየሆኑ መምጣታቸዉን ገልጸዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተላላፊ ባልሆኑ ህመሞች ዙሪያ የ 5 ዓመት ዕቅድ አዉጥቶ እየሰራ ነዉ የሚሉት ዶክተር ደረጄ፤ በዚህ ስር ትኩረት ከተሰጣቸዉ ጉዳዮች መካከል የሚጥል ህመም አንዱ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዓለም ዓቀፍ ደረጃ 50 ሚሊየን ሰዎች ከሚጥል ህመም ጋር የሚኖሩ ሲሆን፤ 80 በመቶ የሚሆኑት የሚገኙት በዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸዉ አገራት ዉስጥ ነዉ፡፡
ጤና ሚኒስቴር አደረግኩት ባለዉ ጥናት በአገራችን ወደ 1.2 ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎች ከሚጥል ህመም ጋር ይኖራሉ፡፡
ፕሮግራሙን ጤና ሚኒስቴር በሚጥል ህመም ዙሪያ ከሚሰራዉ ከኬር ኤፕለፕሲ ኢትዮጵያ ጋር በመሆን ያዘጋጀዉ ሲሆን፤ የዚህኛዉ ዓመት መሪ ቃል ‹‹ የእኔ የሚጥል ህመም ጉዞ›› የሚል ነዉ፡፡
10ኛዉ ብሄራዊ የሚጥል ህመም ወር ለተከታታይ አንድ ወር የሚከበር መሆኑም ተገልጿል፡፡
እስከዳር ግርማ
የካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም
