የሐማስ ታጣቂ ክንፍ ቃል አቀባይ ቡድኑ በቅርቡ ሊለቃቸው ያሰባቸውን ታጋቾችን ለጊዜው እንደማይለቅ ተናግረዋል።
በጋዛ የሚገኙ ሶስት ታጋቾች በሚቀጥለው ቅዳሜ ይለቀቃሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር። እስራኤል ደግሞ ፍልስጤማዊያን እስረኞችን እንደምትለቅ ይጠበቃል።
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ የሐማስን ድርጊት “የተኩስ አቁም ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ የሚያፈርስ ነው” ብለውታል።
የእስራኤል የቅርብ አጋር የሆኑት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሁሉም ታጋቾች በሚቀጥለው ቅዳሜ የማይለቀቁ ከሆነ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሊሰረዝ ይገባል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
“ሁሉም ታጋቾች ቅዳሜ ቀትር መለቀቅ አለባቸው። ሁሉም። አንድ ወይም ሁለት አሊያም ሶስት አራት ሳይሆን፤ ሁሉም” ብለዋል።
“ይህ የኔ አስተያየት ነው” ያሉት ትራምፕ “እስራኤል የፈቀደችውን ማድረግ ትችላለች” የሚል ሐሳብ ሰጥተዋል።
ሐማስ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7/2023 ባደረሰው ጥቃት የታገቱ 73 ሰዎች እና ከአስር ዓመት በፊት የተወሰዱ ሶስት ታጋቾች አሁንም በጋዛ ይገኛሉ።
ታጋቾቹ የማይለቀቁ ከሆነ “ገሀነም ይወርዳል” ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው ጋዛን በባለቤትነት ማስተዳደር እንደምትፈልግ መናገራቸው ይታወሳል።
ሐማስ ስለትራምፕ አስተያየት የሰጠው ምላሽ የለም።
የካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም
