የኢትዮጵያ የአእምሮዊ ንብረት ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ኤሊያስ መሀመድ ተቋማቸዉ የመመዝገብ እና የመጠበቅ ሀላፊነት ያለዉ ቢሆንም የአእምሮ ንብረት ዉጤቶቹ ስራ ላይ አለመዋል ትልቅ ክፍተት ሆኗል ብለዋል።
ለዚህም የፈጠራ ሥራ አመንጪዎች ለገጠማቸዉ የገንዘብ እጥረት ባለስልጣኑ ለመፍታት የሚሰጠዉ አገልግሎት ባይኖርም የድጋፍ እና የትብብር ደብዳቤዎቹን እያደረገ መሆኑን ሀላፊዉ ለጣቢያችን ገልፀዋል።
ባንኮች የአእምሮ ንብረቶች ዉጤቶችን በመያዥነት በመጠቀም የአምስት በመቶ የብድር አገልግሎት እንዲሰጡ የወጣ አዋጁ መኖሩን ሀላፊዉ ጠቁመዋል።
አንድ የፈጠራ ስራ በሳይንሳዊ እና ህጋዊ መንገድ የዋጋ ትመና በመመዘን እንዲሁም ወደ ስራ ሲገባ የሚያስገኘዉን ጠቀሜታ በማስላት ብድር የሚያገኙበት አካሄድ ያለዉ ነዉ ተብሏል።
የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ ኤሊያስ መሀመድ ምዝገባ የተደረገላቸዉን የፈጠራ ዉጤቶች የማስተዋወቅ ስራዎችን እየሰራ ቢገኝም የፋይናንስ ተቋማቱን ሚና መተካት የሚችል አይደለም ብለዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ የአእምሮአዊ ንብረት ባለስልጣን የአእምሮአዊ ንብረት ምዝገባዉን በዲጂታል መንገድ ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው የቴክኖሎጂ አሰራሮች ለማሟላት ዉስንነቶች መኖራቸዉ ተገልፆል።
ቁምነገር አየለ
የየካቲት 5 ቀን 2017 ዓ.ም
