ብረሰልስ ተጨንቃለች፤ ኬቭም ግራ ተጋብታለች ፤ለንደን ፤ፓሪስና በርሊንም ሳንዘጋጅ ተበላን እያሉ ነዉ
አዉሮፓና አሜሪካ በአንድ ሲሰልፉ አለምም ጤናዋ የተሸለ ይሆናል የሚለዉን የቶኒ ብሌርን ንግግር ዶናልድ ትራምፕ አፈር ድሜ አብልተዉታል፡፡
ሰዉየዉ እንደፎከሩት ነጩ ቤተመንግስት ሲገቡ የነበረዉን እንዳልነበር፤ ያልነበረዉን ደግሞ እዉን እያደረጉ ዩክሬንን እርቃኗን ለሩሲያ አጋልጠዉ ሰጥተዋል፡፡
የአዉሮፓ መሪዎችንም እንቅልፍ አልባ ሌሊቶችን እንዲሳልፉ አድርገዋቸዋል፡፡
የምድሪቱ ብርቱ የጦር ጎራ የሆነዉን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶን መፈረካከስ ጀምረዋል፡፡
የአዉሮፓ ኃያላንም ኔቶን የሚተካ ሌላ ኔቶ እንፍጥር እስከማለት ደርሰዋል፡፡
ፖሪስ የህልዉና ጉባኤ ብላ የሰየመችዉን ወሳኝ ስብሰባ ደግሳለች፡፡
ለንደንም ኬቭን ለፑቲን አሳልፌ የምሰጥበት ሞራሉ የለኝም በሚል ጦሯን ወደ ዩክሬን እንድምታዘምት በጥቅላይ ሚኒስትሯ በኩል ይፋ አድርጋለች፡፡
ትራምፕም ባለቤቷ ዩክሬንን ሳይጋብዙ ከሩሲያ ጋር ብቻ ለመምከር ልዑካናቸዉን ወደ ሳዉዲ አረቢያ መላካቸዉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሞስኮም አንጋፋዉን ዲፕሎማት የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ሰርጌ ላቭሮቭን ወደ ሪያድ መላኳ ተሰምቷል፡፡
የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም አሜሪካና ሩሲያ በሚያደርጉት የሰላም ንግግር አገራቸው አለመጋበዟን የዩክሬን መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊ አስታዉቀዋል፡፡
የአውሮፓ መሪዎችም የሰላም ንግግሩ ላይ እንዲሳተፉ ባለመጋበዛቸዉ ፓሪስ ውስጥ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት በአስቸኳይ ባዘጋጁት የመሪዎች ስብሰባ ላይ ተገኝተዋል፡፡
አህጉሪቱ ከሰላም ንግግሩ ውጪ ተደርጋለች የሚለው ስጋት እየጨመረ ይገኛል።
አሁን የፖለቲካ ልሂቃን እንፈደሚሉት ነገሮች ተገለባብጠዋል፡፡
ዘመናትን የተሻገረዉ የአዉሮፓና የአሜሪካ ቤተሰባዊ ግንኙነትም ንፋስ ገብቶታል፡፡
ኮሜዲያኑ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪም ጆ ባይደን ሆይ ማረኝ ተመልስ ናልኝ የሚሉበት ዘመን ላይ ደርሰዋል፡፡
ብረሰልስ ተጨንቃለች፤ ኬቭም ግራ ተጋብታለች ፤ለንደን ፓሪስና በርሊንም ሳንዘጋጅ ተበላን እያሉ ነዉ፡፡
የክሪሚሊኑ አለቃ ቭላደሚር ፑቲን ግን ይብላኝ ለእናንተ እንጅ እያሉ ከትራምፕ ጋር ፊት ለፊት ለመናጋገር ሻንጣቸዉን እየሸከፉ ነዉ፡፡
አሁን በሳዉዲዉ የሰላም ንግግር ላይ ለሶስት አመታት እንደ ጅረት ዉሃ ለዩክሬን የጦር መሳሪያና ገንዘብ ሲያንቆረቁሩ የነበሩት የአዉሮፓ ሓያላንን እንዳይገኙ ተከልክለዋል፡፡
ወደ 80 አመት እየተንደረደረ የሚገኘዉ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶም ትልቅ አደጋ ዉስጥ ወድቋል፡፡
ከምንም በላይ ግን ሶስት አመት ሙሉ በሩሲያ ጦር የነደደችዉ፤ 18 በመቶ የሚሆነዉን ግዛቷን በፑቲን የተቀማችዉ አገረ ዩክሬን በትራምፕ አካሄድ እጣፈንታዋ ምን ሊሆን ይችላል የሚለዉ የእሷ ብቻም ሳይሆን የመላዉ አዉሮፓ ስጋትና ጥያቄ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ይባስ ብሎ ዶናልድ ትራምፕ ሩሲያ የኔቶ ስጋት አይደለችም ይህ የፈሪዎች ሃሳብ ነዉ ማለታቸዉን ተከትሎ ለብረሳለስ አለቆች ዱብዳ ሆኗል፡፡
ሰዉየዉ በዚህ አላበቁም “እናንተ አዉሮፓዉያን ሆይ ዩክሬንን መርዳት ከፈለጋችዉ መሳሪያ ከእኛ እየገዛችሁ መርዳት ትችላላችሁ እኛ ግን ትርፍ ለሌለዉ ጦርነት ገንዘባችንን አናባክን”ማለታቸዉን አርቲ ኒዉስ ዘግቧል፡፡
ትራምፕ ዩክሬንን የሰጠንሽን ገዘብ መልሺልን ማለትም ጀምረዋል፡፡
ጦርነቱ ከተጀመር ወዲህ ባለፉት 3 አመታት ዉስጥ ብቻ አሜሪካ ሶስት መቶ ቢሊዮን ዶላር ለዩክሬን ድጋፍ እንዳደረገች የገለጹት ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሁን ላይ ዩክሬን በአይነት 5 መቶ ሚሊዮን ዶላር እንድትመልስ አሳስበዋል፡፡
የደህንነት አማካሪያቸዉ ማይክል ዋልዝ ኬቭ የአሜሪካዉያንን እዳ መክፈል አለባት ብለዋል፡፡
ይህ ማለት ደግሞ የሰዉ እጅ ለምትጣበበቀዉና በጦርነት ለወደመችዉ ኬቭ ሌላ የራስ ምታት ነዉ፡፡
ፈረንሳይ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ የጠሩት ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እንዳሉት የጉባኤዉ አላማ የአዉሮፓን ስጋቶች መቀነስና የዩከሬንን ህልዉና ማስጠበቅ እንዲሁም ለዩክሬን የሚደረገዉን ድጋፍ በተመለከተ ነዉ፡፡
ከፓሪሱ ስብሰባ ቀድም ብሎ ደግሞ ከወደ ለንደን የተሰማ ዜና መኖሩ ተዘግቧል፡፡
ይህን ዜና ያበሰሩት የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር ናቸዉ፡፡
ስታርመር ዩክሬን ብቻም ሳትሆን አዉሮፓ አደጋ ዉስጥ ወድቃለች፤ ይህ አደጋ ደግሞ ከብዙ አመታት በኋላ ሊከሰት የሚችል የህልዉና አደጋ ነዉ ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
እናም ይህንን ስጋት ለመከላከል ወታደሮቻችንን ወደ ዩክሬን ለመላክ እንገደዳለን ሲሉ በግልጽ አስታዉቀዋል፡፡
በርግጥ ሰር ኬር ስታርመር ወታደቶቻችንን የምናዘምተዉ ለዩክሬን የፀጥታ ዋስትና ለመስጠት ነዉ ብለዋል፡፡
አሜሪካና አውሮፓ በውጫዊ ጠላት የተነሳ መሀላቸው ንፋስ ሊገባ አይገባም ብለዋል።
በዚህ ሳምንት መጨረሻ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ‘የተባበሩት አውሮፓ ጦር’ እንዲቋቋም ጠይቀው ነበር።
ይህም የሆነው አሜሪካ ለዩክሬን ከዚህ በኋላ ወታደራዊ ድጋፍ እንደማታደርግ ከገለጸች በኋላ ነው።
ዘለንስኪ በሙኒክ የሰላም ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ በጉባኤው ያሰሙት አስደጋንጭ ሐሳብ ከዚህ ወዲያ አሜሪካና አውሮፓ እንደከዚህ ቀደሙ እንደማይቀጥሉ ፍንጭ ሰጥቷል ብለዋል።
ስለዚህም አውሮፓ አህጉር ከአዲሱ እውነታ ጋር ራሱን ማስታረቅና ለአዲሱ እውነታ አይኑን መግለጥ ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል።
እናም ዘለንስኪ እንደለመዱት አኩርፋዳቸዉ ይዘዉ የድረሱልኝ ጥሪያቸዉን እያሰሙ የአዉሮፓን ከተሞች ማካለል ጀምረዋል፡፡
ትራምፕና ፑቲን ለአለም ሰላም ስራችንን እየሰራን ነዉ እያሉ ነዉ፡፡
ከሪያዱና ከፓሪሱ ስብሰባ በኋላ የሚሆነዉን ለማየት እድል ቢሰጥም
የቀድሞዉ የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ለአለም ሰላም ሁሌም የአሜሪካና የአዉሮፓ ወዳጅነት ወሳኝ ነዉ ቢሉም እሱ ዛሬ ላይ እየተቀበረ ይመስላል፡፡
ምክንያቱም ሰዉየዉ ትራምፕ መጥተዋልና፡፡
አባቱ መረቀ
የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም
