የሱዳን የሽግግር መንግስት ምክር ቤት ሊቀመንበር አብዱል ፈታህ አል ቡርሀን ከአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ጋር በዳርፉር ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም የተባበሩት መንግስታት እና የአፍሪካ ህብረት የዳፉርን ሰላም ለማስከበር የገቡት የጋራ ተልዕኮ (UNAMID) ሰላም አስከባሪ ጦር እስከመጭው ጥቅምት ድረስ ለቆ እንዲወጣ መስማማታቸውን ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል።
አል-ቡርሃን በዳርፉር የሰፈረው የሰላም አስከባሪ ጦር ለቆ እንዲወጣ የተወሰነውን ውሳኔ ቢደግፉም በሱዳን የሽግግስር መንግስት ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን አንዲሁም ያለው ችግር ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ አንዲፈታ የተሰጠው ተልዕኮ ላይ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡
ሱዳን የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የሱዳንን የሽግግር መንግስቱን እንዲደግፍ እና ተጨማሪ ሰላም አስከባሪ ጦር በሁሉም የሱዳን ስፍራዎች እንዲያሰማራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብደላ ሀምዶክ መጠየቃቸው ይታወሳል።
ይሁንና የሱዳን የሽግግር መንግስት ምክር ቤት ሊቀመንበር አብዱል ፈታህ አል ቡርሀን ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብደላ ሀምዶክን አስተያየት እንደሚቃወሙት ተናግረዋል።
በዳርፉር የነበረው የሰላም አስከባሪ ጦር ቦታውን ለቆ እንዲወጣ ቢወሰንም በአካባቢው ያለውን ሰላም ለማስጠበቅ ግን ፖሊስንም ጭምር ያከተተ ሀይል በቦታው መሰማራት አንዳለበት የተባበሩት መንገስታት ድርጅት እና እንግሊዝ ሀሳብ ማቅረባቸውም ተነግሯል፡፡
በሱዳን ዳርፉር አካባቢ በ1999 ዓ.ም አንስቶ በተፈጠረው ግጭት የመንግስታቱ ደርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እና አፍሪካ ህብረት በጋራ ሰላም አስከባሪ አሰማርቷል።
በዚህ ስፍራም በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎችን ለመጠበቅ ከ50 በላይ የዓለማችን አገራት የተውጣጡ ከ20 ሺህ በላይ ሰላም አስከባሪ ጦር ያሰማራ ሲሆን ኢትዮጵያ ከ5 ሺህ በላይ ጦር በማዋጣት ቀዳሚ አገር ነበረች።
አሜሪካ እና ሌሎች አገራት ለሰላም አስከባሪው ጦር የሚከፈለ ክፍያዎችን በመቀነሳቸው ምክንያት አሁን ላይ በስፍራው የሚገኘው የሰላም አስከባሪ ጦር ቁጥር ቀንሷል።
ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን ይቀላቀሉ።
በትግስት ዘላለም
ግንቦት 19 ቀን 2012 ዓ.ም
