የአውሮጳ ኅብረት በሩስያ ላይ የጣለውን ማዕቀብ ለማሻሻልም ሆነ ለማንሳት የሞስኮ ኃይሎች ከዩክሬን መውጣት አንዱ ዋነኛ ቅድመ ሁኔታ እንደሚሆን አስታወቀ።
የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ቃል አቀባይ ማዕቀቡ እንዲነሳ ወይም እንዲሻሻል ምክንያት የሌለው ያሉትን ጦርነት በዩክሬን የምታካሂደው ሩስያ ወታደሮቿን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ከዩክሬን አጠቃላይ ግዛት ማስወጣት ይኖርባታል ብለዋል።
የኅብረቱ አባል ሀገራት በሩስያ ላይ ከዚህ ቀደም የጣሏቸውን ሁለት ማዕቀቦች ባለፈው ጥርና በመጋቢት መጀመሪያ ላይ ለተጨማሪ ስድስት ወራት አራዝመዋቸዋል።
በማዕቀቦቹ ላይ ለውጥ ለማድረግ ደግሞ የ27ቱም አባል ሀገራት ሙሉ ስምምነት ያስፈልጋል።
ሩሲያና ዩክሬን በጥቁር ባህር ላይ ላይ የሚያከሂዱትን ውጊያ ሊያቆሙና አንዱ ባንዱ መሰረተ ልማትናት ኢነርጂ ተቋሞች ላይ ጥቃት ላለመፈጸም ትናንት በተናጠል መስማማታቸውን አሜሪካን አስታውቃለች።
ዋሽንግተን በበኩልዋ በሞስኮ ላይ ከጣለችው ማዕቀብ የተወሰነውን ማንሳቱን እንደምትገፋበት ከሩስያ ጋር በደረሰችበት ውል ላይ መስማማቷን አስታውቃለች።
መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓ.ም
