መንግስት ጠንካራና እና በአግባቡ የተደራጀ የፋይናንስ ስርአት በመዘርጋት ከታክስና ታክስ ካልሆኑ ፣ ከእርዳታ ፣ ከብድር እና ከሌሎች ምንጮች የሚሰበሰብ ሃብት ወደ አንድ ቋት የሚሰበሰበው ትሬዠሪ ሲንግል አካውንት በትግበራ ላይ መሆኑ ተገልጿል።
ይህ የአሰራር ስርዓት በበርካታ የባንክ ሂሳቦች ተበታትነው የሚገኙ የመንግስት ገንዘቦችን ወደ አንድ ቋት የሚያመጣ መሆኑን አስታውቀዋል።
በገንዘብ ሚኒስቴር የትሬዠሪና የመንግስት ሂሳብ መምሪያ ሀላፊ ነጠሩ ወንድወሰን፤በተበታተነ የሂሳብ አያያዝ የሚከሰቱ ችግሮችን በማቃለል ዘመናዊ የመንግስት ጥሬ ገንዘብ አያያዝ አስተዳደር እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።
ሃላፊዋ መንግስት የገንዘብ እንቅስቃሴውን ለማዘመን በጀመረው ጥረት ሂደቱን በዲጂታል ስርአት ለመለወጥ አበረታች ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የመንግስትን ሃብት ወጪ ቆጣቢ ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ በሆነ ስርአት ማስተዳደር ሀገራዊ ግዴታችን ነው ያሉት።
ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ የትሬዥሪ ነጠላ አካውንት ስርአት ቁልፍ ሚና አለው ብለዋል።
በዚህም ዘመናዊ የመንግስት ጥሬ ገንዘብ አያያዝ ደግሞ ቀልጣፋ፣ ውጤታማ፣ ግልፅ እንዲሁም ተጠያቂነት የሰፈነበት የመንግስት የፋይናንስ አስተዳደር እንዲኖር ያስችላል ነው ያሉት።
በኢትዮጲያ ብሔራዊ ባንክ የሞኒተሪ ፖሊሲና ትንተና ሀላፊ ወይንሸት ዘበርጋ በበኩላቸው፤መንግስት ለአጭር ጊዜ ብድሮች የሚያወጣቸውን ወጪዎች በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የተናበበ የገንዘብና ፊሲካል ፖሊሲ እንዲኖር ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለውም የሞኒተሪ ፖሊሲና ትንተና ሀላፊ ወይንሸት ዘበርጋ አስረድተዋል።
ልኡል ወልዴ
መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓ.ም
