የደቡብ ሱዳን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንት ሪየክ ማቻር እስር ለአምስት ዓመታት የተካሔደውን የርስ በርስ ጦርነት ያቆመውን የሰላም ሥምምነት በቀጥታ እንዳፈረሰ ፓርቲያቸው አስታወቀ።

የደቡብ ሱዳን መከላከያ ሚኒስትር እና የሀገሪቱ የብሔራዊ ጸጥታ ኃላፊ ወደ ሪየክ ማቻር መኖሪያ ቤት በኃይል ገብተው የእስር ማዘዣ መስጠታቸውን የሱዳን ሕዝቦች ነጻ አውጪ ንቅናቄ በተቃውሞ (SPLM-IO) ገልጿል።

በጁባ በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ከባለቤታቸው ጋር በቁም እስር ላይ የሚገኙት ማቻር “ዋይት አርሚ” የተባለ ታጣቂ ቡድን በመደገፍ መወንጀላቸውን የሱዳን ሕዝቦች ነጻ አውጪ ንቅናቄ በተቃውሞ (SPLM-IO) ከፍተኛ አመራር የሆኑት ሪትዝ ሞች ታንግ ያወጡት መግለጫ ይጠቁማል።

ዋይት አርሚ ተብሎ የሚጠራ የኑዌር ጎሳ ታጣቂ ቡድን ከኢትዮጵያ ድንበር በ30 ኪሎ ሜትር ገደማ በምትርቀው ናስር የተባለች ከተማ ከደቡብ ሱዳን ጦር የተዋጋ ነው።

የሱዳን ሕዝቦች ነጻ አውጪ ንቅናቄ በተቃውሞ (SPLM-IO) ምክትል ኦዬት ናታንዬል ፒዬሪኖ እንዳሉት የሪየክ ማቻር እስር በጎርጎሮሳዊው ከ2013-2018 የተካሔደውን ጦርነት ያቆመውን የሰላም ሥምምነት የሻረ ነው።

የማቻር እስር “በቀጥታ የሰላም ሥምምነቱን አፍርሶታል። በዚህም ምክንያት የደቡብ ሱዳን የሰላም እና የመረጋጋት ተስፋ አሁን ከፍተኛ አደጋ ላይ ወድቋል” ብለዋል።

በደቡብ ሱዳን የሰፈረው የተባበሩት መንግሥታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ሀገሪቱ ወደ መጠነ ሰፊ ግጭት ልትመለስ እንደሆነ አስጠንቅቋል። ተልዕኮው እንዳለው “ይህ ደቡብ ሱዳንን ከማውደም ባለፈ ለመላ ቀጠናው ተጽዕኖ ይኖረዋል።”

መጋቢት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *