ለሳምንታት በዩክሬን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ሲሞክሩ የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ በሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን “እጅግ ተበሳጭቻለሁ” አሉ።
ኤንቢሲ ከተባለው ጣቢያ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአሜሪካው ፕሬዝደንት፤ ፑቲን የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ተዓማኒነት ላይ ጥቃት በመሰንዝራቸው መናደዳቸውን ተናግረዋል።
ትራምፕ፤ ፑቲን የተኩስ አቁም ስምምነት ካልፈረሙ ከሩሲያ ነዳጅ የሚገዙ ሀገራት ላይ የ50 በመቶ ታሪፍ ለመጣል ዝተዋል።
“በዩክሬን ያለውን ደም መፋሰስ ለማስቆም እኔ እና ሩሲያ ከስምምነት የማንደርስ ከሆነ እና የሩሲያ ጥፋት ነው ብዬ ካሰብኩ – ላይሆንም ይችላል – ከሩሲያ የሚወጣ ነዳጅ ላይ ታሪፍ እጥላለሁ” ብለዋል።
ትራምፕ የሰጡት አስተያየት በሩሲያ ጉዳይ ያላቸው አቋም መለወጡን የሚያሳይ ነው ተብሏል።
ዋይት ሐውስ ፕሬዝደንቱ ባሰሙት ንግግር ዙሪያ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።
አውሮፓውያን መሪዎች ትራምፕ በዩክሬን የተኩስ አቁም ስምምነት ጉዳይ የፕሬዝደንት ፑቲንን አቋም እያንፀባረቁ ነው የሚል ትችት ያሰማሉ።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ትራምፕ ፕሬዝደንት ዜሌንስኪን ወደ ኦቫል ኦፊስ ጠርተዋቸው በቀጥታ በተላለፈ ስርጭት እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተው እንደነበር ይታወሳል። በሌላ በኩል ደግሞ የሩሲያውን ፕሬዝደንት ስም ሲያወድሱ ተሰምተዋል።
አሜሪካ በዩክሬን ተኩስ አቁም ጉዳይ ሩሲያን ስትወቅስ እና ዛቻ ስታሰማ ይህ የመጀመሪያው ሲሆን ከሩሲያ የሚመጣው ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ይጠበቃል።
መጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም
