እስራኤል በምሥራቅ ጋዛ በመኖርያ ሕንጻ ላይ በፈጸመችው ጥቃት ሕጻናትን ጨምሮ 29 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በአካባቢው የሚገኝ ሆስፒታል ገለፀ።
በሃማስ የሚመራው የሲቪል መከላከያ ኤጀንሲ በበኩሉ ማክሰኞ ማለዳ የጦር አውሮፕላኖች ሼጃያ በሚባል ስፍራ በሚገኘው አል ሃዋሺ መስኪድ አቅራቢያ የሚገኙ ቦታዎችን ዒላማ አድርገዋል ብሏል።
በእስራኤል የአየር ጥቃት መጀመሪያ ላይ 23 ሰዎች መገደላቸው የተገለፀ ቢሆንም፣ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ሌሎች በርካታ ሰዎችን ከፍርስራሹ ውስጥ ሟቾችን ለማውጣት ፍለጋ ላይ በመሆናቸው ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል ተነግሯል።
ረቡዕ ምሽት አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር በይፋ ሳይገለፅ፣15 አስከሬኖች መገኘታቸው ብቻ ይፋ ሆኗል።
የእስራኤል ጦር በአካባቢው ጥቃቶችን በማቀድ እና በማስፈፀም ኃላፊነት ያለውን “ከፍተኛ የሃማስ አሸባሪ” መትቻለሁ ብሏል።
በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል “ዒላማቸውን ለይተው የሚመቱ የጦር መሳሪያዎችን” ከመጠቀም ጀምሮ በርካታ እርምጃዎች ተወስደዋል ሲልም ገልጿል።
ወታደራዊ ቡድኑ፣ሃማስ ሆን ብሎ ሰላማዊ ሰዎችን እንደ ጋሻ ይጠቀማል በማለት ሀማስን በዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ከስሷል።
ባለፉት ሦስት ሳምንታት ውስጥ ተጨማሪ 390,000 ሰዎች ተፈናቅለዋል።
ከግዛቱ ውስጥ ሁለት ሦስተኛው አሁን በእስራኤል ጦር “የማይደረስበት” ስፍራ ተብሎ የተለየ ወይም የልቀቁ ትእዛዝ የተሰጠበት መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይናገራል።
ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በፈጸመው ጥቃት 1,200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።
እስራኤል በጋዛ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት ከ50 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ሕፃናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።
እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የተቀናጀ እና የማያባራ ጥቃት ሁለት ሦስተኛው የጋዛ ሕንጻዎች መውደማቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።
ሚያዚያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም
