የሀንጋሪ ፓርላማ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንን እና የጥምር ዜጋ ባለቤቶችን መብት የሚገድቡ ሕጎችን ጨምሮ ሌሎች ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያዎች አድርጓል።
መንግሥት ማሻሻያዎቹ የተደረጉት የሕፃናትን አካላዊ እና ሞራላዊ ዕድገት ለመጠበቅ ነው ብሏል።
በአዲሱ ሕግ መሠረት የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን በአደባባይ መሰባሰብ አይችሉም።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከፓርላማው ውጭ ተገኝተው ተቃውሞ አሰምተዋል። የመብት ተሟጋች ቡድኖች ውሳኔው ሀንጋሪ “ነፃነት ወደሌለው መንግሥት ማቅናቷን የሚያሳይ ነው” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክተር ኦርባን ባለፈው መጋቢት ተቺዎቻቸውን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት “የፋሲካ ሰሞን ፅዳት” እናደርጋለን ብለው ነበር።
የገዢው ፊዴዝ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ 140 የሕዝብ እንደራሴዎች ድጋፋቸውን ሲገልፁ 21 ተቃውሞ ተሰምቷል።
በአዲሱ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ መሠረት የጥምር ዜጋ ባለቤት የሆኑ ሀንጋሪያዊያን ለሀገሪቱ ደኅንነት አደጋ ናቸው ተብሎ ከታሰበ ዜግነታቸውን ሊነጠቁ ይችላሉ።
ገዢው ፓርቲ እንደሚለው አዲሱ ሕግ ዒላማ ያደረገው “አጠራጣሪ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን፣ ገንዘብ የሚገዛቸው ፖለቲከኞችን እና ራሳቸውን ነፃ ብለው የሚጠሩ ሚድያዎችን” በገንዘብ የሚደግፉ ሰዎችን ነው ብሏል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ሚያዚያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም
