የሜትር ታክሲ አገልግሎትን በመስጠት ላይ የሚገኘው ያንጎ፤ አሽከርካሪዎቹ የ ኢንሹራንስ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ስምምነት መፈረሙን አስታውቋል።

ያንጎ ድርጅት አሽከርካሪዎቹ የሙሉ አረቦን ፕሪሚየም ኢንሹራንስ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን የሦስትዮሽ ሥምምነት ከንብ ባንክ እና ንብ ኢንሹራንስ ጋር ተፈራርሟል።

ሥምምነቱም የሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ ብቻ የነበራቸውን የያንጎ አሽከርካሪዎች ሙሉ የኢንሽራንስ ክፍያ ለንብ ኢንሹራንስ እንዲከፈል የሚያደርግ መሆኑ ተጠቅሷል።

በሥምምነት ሥነ ስርዓቱ ወቅት የጂ ቱ ጂ አይቲ ሶሉሽን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ መሃሪ እንደተናገሩት፤ የሦስትዮሽ ስምምነቱ የያንጎ አሽከርካሪዎች የሚያጋጥማቸውን ፈተናዎች በመቅረፍ ተመጣጣኝ እና ተደራሽ የሆነ አጠቃላይ የመኪና ኢንሹራንስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ አብዛኛው የያንጎ አሽከርካሪዎች ለተሸከርካሪዎቻቸው ጥበቃ በሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ ብቻ ይተማመናሉ ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ በዚህም ምክንያት አደጋ በሚደርስበት ወቅት ዋና የገቢ ምንጫቸውን ለጥገና በማውጣት ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ለችግር የሚዳርጉበት አጋጣሚ መኖሩን አንስተዋል።

በመሆኑም የዛሬው ሥምምነት አሽከርካሪዎች በአንድ ጊዜ ሳይሆን በየወሩ አረቦን መክፈል የሚችሉበትን ዕድል የፈጠረ በመሆኑ፤ አሽከርካሪዎች ላይ የሚደርሰውን የገንዘብ ጫናን በእጅጉ እንደሚቀንስ ተናግረዋል።

ሐመረ ፍሬው

ሚያዚያ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *