ፓኪስታን ሦስት የጦር ሰፈሮቼ ላይ በሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሚሳኤሎች ጥቃት አድርሳለች ስትል ሕንድ ብትከስም ኢዝላማባድ ግን ውንጀላውን ውድቅ አድርጋለች።
የሕንድ ጦር አገሪቱ በምታስተዳደረው የካሽሚር ግዛት በሚገኘው በጃሙ እና በፑንጃብ ግዛት በሚገኘው ፓታንኮት የጦር ሰፈሮቿ ፓኪስታን የሞከረችውን ጥቃት ማክሸፉን ገልጿል።
በሕንድ ቁጥጥር ስር በምትገኘው የካሽሚሯ በጃምሙ ከተማ ሐሙስ አመሻሹ ላይ ፍንዳታዎች መሰማታቸውን እና መብራት መቋረጡ ተዘግቧል።
የፓኪስታን የመከላከያ ሚኒስትር ከጥቃቱ ጀርባ እጃቸው እንደሌለበት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“እስካሁን ጥቃት አልፈጸምንም። ምንም አላደረግንም። ጥቃት አድርሰን ደግሞ አንክድም” ሲሉ ካዋጃ አሲፍ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ሐሙስ ዕለት ሕንድ የፓኪስታንን የአየር መከላከያ መምታቷን እና ኢዝላማባድ ረቡዕ ምሽት ሕንድ ውስጥ የሚገኙ ወታደራዊ ዒላማዎችን ለመምታት ያደረገችውን ሙከራ “ማክሸፏን” አሳውቃለች።
ሕንድ ረቡዕ ዕለት በፓኪስታን እና በፓኪስታን ቁጥጥር ስር በሚገኘው ካሽሚር ውስጥ የሚገኙ ዒላማዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ፓኪስታን ድርጊቱን ሌላ “የጥቃት አባባሽ ድርጊት” ስትል ጠርታዋለች።
ሕንድ የፈጸመችውን ጥቃት ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የዓለም መሪዎች መረጋጋት እንዲሰፍን ጥሪ አቅርበዋል።
በድንበር አካባቢ የሚፈጸመው ጥቃት የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤቶቹን ወደ ከፍተኛ ግጭት ሊያመራቸው ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
ይህም ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በሁለቱ አገራት መካከል የከፋው ግጭት ተደርጎ ተወስዷል።
ግንቦት 1 ቀን 2017 ዓ.ም
