ቻይና እና አሜሪካ በስዊዘርላንድስ ባደረጉት ድርድር ቁልፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የተሻለ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ገለፁ።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ዋና ጸሐፊ ስኮት ቤሴት ውይይቱን “ገንቢ እና ውጤታማ” ሲሉ የገለፁት ሲሆን የቻይናው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሂ ሊፌንግ በበኩላቸው ንግግሮቹ “በጥልቀት” እና “በመግባባት” የተካሄዱ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ሁለቱ አገራት ዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ ታሪፍ ከቻይና የሚገቡ ምርቶች ላይ ከጣሉ በኋላ ቅዳሜ እና እሁድ በዝግ ሲወያዩ ቆይተዋል።
ይህ ሁለቱ አገራት በስዊዘርላንድስ ያካሄዱት ውይይት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይና የሚገቡ ምርቶች ላይ 145 በመቶ ታሪፍ ከጣሉ እና ቻይና በምላሹ በአሜሪካ ምርቶች ላይ 125 በመቶ ታሪፍ ከጣለች በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ፊት ለፊት የተካሄደ ድርድር ነው።
ይህ ግዙፍ ታሪፍ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ገበያዎች መካከል አለመረጋጋትን የፈጠረ ሲሆን ዓለም አቀፍ ግሽበት ያስከትላል የሚል ፍርሃት ቀስቅሷል።
ሁለቱ አገራት ስለተነጋገሩባቸው ዝርዝር ጉዳዮች ሰኞ ዕለት በሚሰጡት የጋራ መግለጫ ላይ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ግንቦት 4 ቀን 2017
