ስምምነቱ የተደረሰው ትናንት በ 78 ተኛው የዓለም የጤና ጉባኤ የጸደቀው ለሦስት ዓመታት ከተካሄደ ያላሰለሰ ድርድር በኋላ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶክተር ቴዎድሮስ አንድሃኖም ገልጸዋል።
«ዓለም አሁን ደኅንነቱ አስተማማኝ ነው» ያሉት ዳይሬክተሩ ለዚህም የዓለም የጤና ድርጅት አባል ሃገራት የሰጡትን አመራር፣ ትብብር እና ቁርጠኝነት አመስግነዋል።
ስምምነቱ ለማኅበራዊ ጤና ዘርፉ፤ ለሳይንስ እና ለዘርፈ ብዙ እርምጃዎች ድል መሆኑን ያመለከቱት የዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር፣ በጋራ ዓለምን ከወረርሽኝ ስጋት በተሻለ ለመከላከል እንደሚረዳም ገልጸዋል።
በግርድፍ ትርጉሙ «የወረርሽኝ ስምምነት» የተሰኘው ሃገራት ተግባብተው ያጸደቁት ውል በ124ቱ የድርጅቱ አባላት የድጋፍ፣ ያለምንም ተቃውሞ ነው ተቀባይነት ያገኘው።
በጤናው ዘርፍ የኮቪድ 19 ወረርኝ ከተከሰተበት ወቅት አንስቶ መንግሥታት በከፍተኛ ኃላፊነት በጋራ እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ነው የተገለጸው።
ስምምነቱን በተመለከተም የውሳኔ ሃሳቡን ተግባራዊነት ለማዘጋጀት የዓለም የጤና ጉባኤ የሚወሰዱ እርምጃዎችን ነድፏል።
የሂደቱን ውጤታማነትም በሚቀጥለው ዓመት የዓለም የጤና ጉባኤ ለማየት ወስኗል።
ግንቦት 13 ቀን 2017 ዓ.ም
