የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛዉን ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅቴን ጀምሬያለሁ ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ የቀጣዩን ሀገራዊ ምርጫ ዝግጅትና ተያያዥ ጉዳዮች አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም፤ ዝግጅቱ እየተከናወነ ያለው በ2018 ዓ.ም የሚካሄደውን ሀገራዊ ምርጫ መሠረት አድርጎ ነው ብለዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ባካሄደው ጥናት የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ፕላን ማዘጋጀቱንም አስታውቀዋል፡፡
ለቀጣዩ ምርጫ ግብዓት የሚሆኑ ተሞክሮዎችንና ሊሻሻሉ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መራጭ ብቻ ሳይሆኑ በዕጩነት መሳተፍ የሚችሉበት ጥናት መካሄዱንም አረጋግጠዋል፡፡
ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበው ረቂቅ አዋጅ የምርጫ ሂደቱን ከንክኪ የፀዳ ለማድረግም ውጥን ተይዟል ብለዋል፡፡
ምርጫ ጣቢያዎችን በአግባቡ መለየትና መቆጣጠር የሚያስችል ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለያዩ ክልሎች ወደ 12 ሺህ የሚሆኑ ምርጫ ጣቢያዎችን የማጣራት ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።
የምርጫ ጣቢያ አስፈፃሚዎች ፈተና በኦንላይን እንደሚሰጥ የገለጹት ሰብሳቢዋ፤ በምርጫ ወቅት የእያንዳንዱን ባለሙያ እንቅስቃሴ የሚያመለክት ኦፕሬሽናል ማንዋል መዘጋጀቱ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በፊት ዕጩዎች በምርጫ ክልል ብቻ ይመዘገቡበት የነበረውን አሠራር በማዕከል በኦንላይን መመዝገብ የሚያስችል መተግበሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ማበልጸግ መቻሉንም አንስተዋል፡፡
ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም
