የህክምና መሳሪያዎችን በሊዝ አማራጭ መግዛት የሚቻልበት ስርዓት መኖሩንም ሰምተናል፡፡
ከአገር ዉስጥ መድሃኒት አምራቾች ጋር የ11 ቢሊየን ብር ዉል መታሰሩም ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት በማዕከል የሚፈጸሙ የመድሃኒት እና የህክምና መሳሪያዎች የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን አስታዉቋል፡፡
የአገር ዉስጥ መድሃኒት አምራቾች አቅማቸዉ እስከፈቀደ ማምረት ይችላሉ ተብሏል፡፡
ይህም የአገር ዉስጥ መድሃኒት አምራቾችን ለማበረታታት ያለመ መሆኑን የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በፊት ለመድሃኒት ግዢ ከ2መቶ ቀናት በላይ ጨረታዉ ይቆይ ነበር ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በአዲሱ መመሪያ መሰረት ለአገር ዉስጥ ተጫራቾች 15 ተከታታይ ቀናት እና ዓለም ዓቀፍ ተጫራቾች ደግሞ በ21 ቀናት ጨረታቸዉን ማቅረብ የሚችሉበት ሂደት መፈጠሩን አንስተዋል፡፡
ብዙ ተጠቃሚ የሌላቸዉ ነገርግን አስፈላጊ የሆኑ መድሃኒቶችን በተለይ ደግሞ አንዳንድ የካንሰር መድሃኒቶች ብዙ አምራቾች ስለማይኖራቸዉ ከሌሎች አገራት ጋር በመሆን የጥምር ግዢ መፈጸም እንደሚቻልም በመመሪያዉ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡
በመመሪያዉ መሰረት ከሌሎች አገራት ጋር የጥምር ግዢ መፈጸም፣ የህክምና መሳሪያዎችን በሊዝ አማራጭ መግዛት ፣ የኤሌክትሮኒክስ ልዋጭ ሃራጅ እንዲሁም በኮንትራት ማምረት እንደሚቻል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ለዓለም ዓቀፍ ጨረታ እስከ 3 ቢሊየን ብር ድረስ ፤ ከአገር ዉስጥ አምራቾች ጋር ደግሞ የ11 ቢሊየን ብር ዉል መታሰሩን ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የአገር ዉስጥ አምራቾች እስከ 7 ዓመት የሚደርስ ዉል መፈራረም እና መስራት ይችላሉ ተብሏል፡፡
ከሶስት ዓመት በፊት የአገር ዉስጥ የመድሃኒት አምራቾች የአቅርቦት መጠን 8 በመቶ ነበር ያሉት ዶ/ር አብዱልቃድር፤ አሁን ላይ እስከ 40 በመቶ መድረሱን አንስተዋል፡፡
መመሪያዉ የህመም ዓይነቶች ተለዋዋጭ መሆናቸዉን፣ የመድሃኒቶች መጠን ዝቅተኛ መሆን እንዲሁም ድንገተኛ እና ሰዉ ሰራሽ አደጋዎችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡
መመሪያዉ ከግንቦት 26/2017 ጀምሮ መመሪያ ቁጥር 1066/2017 በመሆን በስራ ላይ ዉሏል ሲል አገልግሎቱ አስታዉቋል፡፡
እስከዳር ግርማ
ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም
