በማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ፤ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አለማየሁ በገላን ቁጥር 2 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው ፈተናውን በማስጀመር ተማሪዎችን አበረታተዋል።
ከተማ አቀፉ የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በሁሉም የመፈተኛ ጣቢያዎች ሰላማዊ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ ከከተማ ጀምሮ እስከ ትምህርት ቤት ድረስ ሂደቱን የሚከታተል የኮማንድ ፖስት አደረጃጀት ከማዋቀር አንስቶ በቂ የፈተና አስፈጻሚዎች ተመልምለው ወደ ስራ መግባታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ተናግረዋል፡፡
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 6,828 ተማሪዎች በ24 የመፈተኛ ጣቢያዎች ከተማ አቀፉን የ2017ዓ.ም የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመውሰድ መመዝገባቸውን የክፍለ ከተማው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከበደ ድሪባ ገልጸው ፈተናው ስኬታማ እንዲሁን የክፍለ ከተማው አስተዳደር አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ስራ መስራቱን አስታውቀዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 71,972 ተማሪዎች በ194 የፈተና ጣቢያዎች የ2017ዓ.ም የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ለመውሰድ መመዝገባቸው እና በቂ ፈታኞች፣ጣቢያ ኃላፊዎች እንዲሁም ሱፐርቫይዘሮችን ጨምሮ የፈተና አስፈጻሚዎች መመደባቸው ቀደም ሲል መገለጹ ይታወቃል።
ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ.ም
