በኢትዮጵያ 90 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ማገዶ፣ ኩበት እና ከሰልን በመጠቀም የዕለት ምግቡን እንደሚያዘጋጅ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቋል።
በሚኒስቴሩ የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጅነር ሱልጣን ወሊ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ጊዜ እንደሀገር ንጹህ የማብሰያ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች ቁጥር 10 በመቶ አይበልጥም።
በሀገሪቱ 90 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ማገዶ፣ ኩበት እና ከሰልን በመጠቀም የዕለት ምግቡን ያዘጋጃል ብለዋል።
በተለይ እናቶችና ህፃናት ምግብ ሲያበስሉ የሚጠቀሙት ማገዶ የሚፈጥረው ጭስ ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተገናኘ ከፍተኛ የጤና ጉዳት ያመጣል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በዘልማድ ለምግብ ማብሰያነት ጥቅም ላይ የሚውሉ ቁሳቁሶች ከእናቶችና ህፃናት ጤና አንፃር የሚያስከትሉት ጉዳት ሊፈተሽ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ይህንንም ለመቅረፍ ብሔራዊ የንጹህ ማብሰያ ፍኖተ ካርታ እየተገበረች መሆኑንም ሰምተናል።
ይህ ፍኖተ ካርታ በታሰበው ልክ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ 93 ሚሊዮን ህዝብ የንጹህ ማብሰያ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
ለዓለም አሰፋ
ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም
