የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማስፈራሪያን ተከትሎ ሩሲያ የብሪክስ አባል ሃገራት ቡድን አላማ ሌሎች ሀገሮችን መጨቆን እንዳልሆነ ገለፀች።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ «ፀረ- አሜሪካን» ያሏቸውን የብሪክስ መርሆች በሚከተሉ ሀገራት ላይ ተጨማሪ 10 በመቶ ቀረጥ እንደሚጥሉ አስጠንቅቀዋል።
የብሪክስ አባል ሀገራት መሪዎች ብራዚል ውስጥ ጉባኤያቸውን በጀመሩበት በትናንትናው ዕለት ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተባለው ማኅበራዊ ድረ ገጻቸው እንደጻፉት ርምጃው ማንኛውንም የብሪክስ ፖሊሲ የሚከተሉትን አይለይም። «ፀረ-አሜሪካን መርሆች» ምን እንደሆኑ በግልጽ ያልተናገሩት ትራምፕ ዛሬ በሀገሪቱ አቆጣጠር ምሳ ሰዓት ላይ ለ15 ንግድ አጋሮች የቀረጥ ጭማሬውን የሚመለከቱ ደብዳቤዎች እንደሚላኩ አስታውቀዋል።
ከትራምፕ ማስፈራሪያ በኋላ „ደቡብ አፍሪቃ ፀረ-አሜሪካዊ „ አይደለችም። ሲሉ የደቡብ አፍሪቃ የንግድ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ለሮይተርስ ተናግረዋል። ቃል አቀባዩ ደቡብ አፍሪቃ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የንግድ ስምምነት የመደራደር ፍላጎት እንዳላትም ተናግረዋል።
ብሪክስ በጎርጎሮሳዊው 2009 ዓ.ም. ባካሄደው የመጀመሪያው ጉባኤ የብሪዚል ፣ ሩስያ ህንድ እና ቻይና መሪዎች ተሳትፈዋል። በኋላም ቡድኑ ደቡብ አፍሪቃን ሲያካትት ባለፈው ዓመት ደግሞ ግብጽ፣ ኢትዮጵያ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ኢራን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የቡድኑ አባላት ሆነዋል። ምንጮች እንዳሉት ሳዑዲ አረብያ ቡድኑን በይፋ መቀላቀልን ትታዋለች ።
ሌሎች 30 ሀገራት ደግሞ የብሪክስ ሙሉ አባል ወይም አጋር የመሆን ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል። በአሁኑ ጊዜ የብሪክስ አባል ሀገራት ከዓለም ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ይወክላሉ ። ከዓለም ምጣኔ ሀብት ደግሞ 40 በመቶው ድርሻ አላቸው ።
ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም
