ኢትዮጵያ ምቹና ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ መሆኗን ለማስተዋወቅ ያለመ ፕላትፎርም ይፋ አድርጌያለሁ ሲል የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

Visit Ethiopia የተሰኘና የዘርፉን በርካታ ችግሮች በመቅረፍ ቱሪዝምን በቴክኖሎጂ በማዘመን፣ ኢትዮጵያ ምቹና ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ መሆኗን ለማስተዋወቅ ያለመ ፕላትፎርም አዘጋጅቻለሁ ሲል የቱሪዝም ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።

የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ Visit Ethiopia የተሰኘውን ፕላትፎርም ሐምሌ 1 ቀን 2017 ዓ.ም በስካይላይት ሆቴል በነበረ የማብሰሪያ ስነ ስርዓት ላይ መርቀው አስጀምረዋል።

ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ ፕላትፎርሙ የቱሪዝም ፀጋዎችን፣ የቱሪስት መዳረሻዎችን፤ የቱሪዝም ምርትና አገልግሎቶችን እንዲሁም፣ የኢትዮጵያን ልዩ የቱሪዝም መገለጫዎች በአንድ Online ስፍራ ለማስተዋወቅ ያስችላል ብለዋል።

የቱሪዝም ዘርፉን ተወዳዳሪነት ከሚፈታተኑ ጉዳዮች አንዱ የቴከኖሎጂ አጠቃቀም አቅማችን ዝቅተኛ መሆን ነው ያሉት ሰላማዊት፣ ይህን ችግር ለመቅረፍ በቱሪዝም እሴት ሰንሰለት ውስጥ የተሰማሩ ቁልፍ የቱሪዝም ተዋንያን በአንድ ስፍራ የሚገናኙበት፣ አገልግሎቶቻቸውንና ምርቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበት፣ የሚሸጡበት፣ እንዲሁም ከቱሪስቶች ጋር የሚገናኙበት ፕላትፎርም ይፋ መደረጉን ተናግረዋል።

የቱሪዝም ሚኒስቴር ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር በትብብ እንዳለሙት የተገለፀው የቴክኖሎጂው ውጤት፣ ህጋዊ የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን ከህገወጦች ለመለየት እና ግልፅና ፍትሃዊ የቱሪዝም ንግድ ለማስፈን ያስችላል ተብሏል፡፡

ፕላትፎርሙ ለቱሪዝም ዘርፍ ባለድርሻ አካላት የቅድመ መረጃ ምንጭ ሆኖ ከማገልገሉም በተጨማሪ ጎብኝዎች ኢትዮጵያን ከጎበኙ በኋላ ስለነበራቸው ቆይታ እና እርካታ ግብረ መልስ የሚሰጡበት ስርዓት እንዳለውም ተገልጿል።

የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር እንደገና አበበ በበኩላቸው ፕላትፎርሙ የቱሪዝም ሃብት በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል።

ፕላት ፎርሙ ከመንግስት የፀጥታ አካላትና ከግል ትራንስፖርት ሰጪዎችም ጋር ለመተባበር፣ መተግበሪያዎቻቸውን በማስተሳሰር ለመጠቀም ክፍት እንደሆነም ገልፀዋል።

አዲስአለም አበበ

ሐምሌ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *