አዋሽ ባንክ ከM-PESA ETHIOPIA ጋር በዲጂታል ቁጠባ እና ብድር አገልግሎት ዙሪያ አብሮ ለመስራት የሚያስችላቸውን የስታራቴጂክ ፓርትነርሺፕ ውል ዛሬ ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም በባንኩ ዋና መስሪያ ቤት ተፈራርሟል።
የአዋሽ ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፀሀይ ሽፈራው በፊርማ ስነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት በዛሬው ዕለት ባንኩ ከM-PESA ETHIOPIA ጋር በተደረገው “እርፍ በኤምፔሳ” የተሰኘው ዲጂታል overdraft የብድር አገልግሎት መተግበሪያ ስምምነት መሠረት ለደንበኞች የዲጂታል ማይክሮ ብድር አገልግሎት ለመስጠት አስፈላጊ የቴክኖሎጂ ማሻሻያዎችን እና ትስስሮችን በማድረግ ወደ ደንበኞቹ ለማቅረብ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገልጸዋል።
የM-PESA ዋና ስራ አስፈፃሚ ኤልሳ ሙዞሊኒ በበኩላቸው ለረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓት ምሰሶ ከሆነው አዋሽ ባንክ ጋር በመተባበር የደንበኞቻችንን የፋይናንስ ደህንነት ለማሻሻል ያለው ዕድል ከፍተኛ ነው ያሉ ሲሆን ይህንን ራዕይ ዕውን ለማድረግ የምንችለው እንደ አዋሽ ባንክ ካሉ ተቋማት ጋር በጠንካራ አጋርነት በመስራት ብቻ ነው ብለዋል ።
አገልግሎቱ አሁን ለሁሉም የM-PESA ደንበኞች ለ90-ቀናት የቀረበ ተደራሽ፣ ቀላል፣ ደህንነ-የተጠበቀ እና ፈጣን ዲጂታል የብድር አገልግሎት ሲሆን በተለይም እያደገ የመጣውን የአነስተ ቢዝነሶችን፣ የቤተሰብ ኃላፊዎችን እና መደበኛ ያልሆኑ ነጋዴዎች የፋይናንስ ፍላጎት ለማሟላት ያለመ ነዉ ተብሎለታል ፡፡
አቤል እስጤፋኖስ
ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም
