በዛሬዉ እለት የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን አካሂዷል።
የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን የዉሳኔ ሀሳብ መርምሮ አፅድቋል።
አዋጁ ከነባሩ አዋጁ 1162/2011ዉስጥ የነበሩ 26 አንቀጾችን ያሻሻለ ሆኖ የቀረበ ነዉ ተብሏል።
አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ሀገራዊ ፓርቲ ሆኖ ለመወዳደር ከ 6 ክልሎች የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብን የሚያስገድድ አንቀፅ ይገኝበታል።
ከዚህ ቀደም ሀገራዊ ፓርቲ ለመሆን የአራት ክልሎች የድጋፍ ፊርማ የሚያስፈልግ ሲሆን ይህንን አንቀፅ ለማሻሻል ያስፈለገበት ምክንያት የተጨመሩ ክልሎች መኖራቸዉን ታሳቢ አድርጎ መሆኑን የዲሞክራሲ ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ ገልፆል።
በዚህ መሰረት ሀገራዊ ፓርቲ ለመመስረት በስድስት ክልሎች የድርጅት አባል ማፍራት እንዳለባቸዉ የሚያደርግ ነዉ።
አንድ የምክር ቤት አባል የሀገራዊ ፓርቲ ምስረታን በየክልሎች የድጋፍ ማሰባሰብ ሂደቱን በተመለከተ ያን ለማድረግ አሁን አመቺ ሁኔታ አለ ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ሌላኛዉ የምክር ቤት አባል በአዋጁ ረቂቅ ላይ ዉይይት በተደረጉባቸዉ መድረኮች ላይ መገኘታቸው ገልፀዉ በመድረኮቹ ተነስተዉ የነበሩ የሀሳብ ግብአቶችን የቀረበዉ ማሻሻያ እንዳላካተተ አንስተዋል።
የምክር ቤት አባሉ አያይዘውም የስድስት ክልሎች የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ የሚለዉ ብዙም የሚያስኬድ አይመስለኝም ብለዋል።
ለምሳሌም ከኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ዉጪ በሁሉም ክልሎች አንድ የፓለቲካ ፓርቲ ቢወዳደር ትርጉም የለዉም 50 በላይ መቀመጫ ማግኘት አይችልም ሲሉ ገልፀዋል።
ከ547 ወንበር ወደ 316 ወንበር ያለዉ በሁለቱ ክልሎች ብቻ ነዉ። ስለዚህ በሁለቱ ክልሎች ብቻ ተወዳድሮ ያሸነፈ ፓርቲ መንግስት መሆን ይችላል ሲሉ ገልፀዋል።
የምክር ቤት አባሉ መታየት ያለበት የክልሎች ብዛት ሳይሆን በፓርላማ ወንበር ቁጥር ባሉ የምርጫ ክልል ዉስጥ መወዳደር የቻለ ፓርቲ ሀገራዊ መቀጠል ይችላል የሚለዉ ታሳቢ ቢደረግ ብለዋል።
ሌላዉ ከእንደራሴዎቹ ምክር ቤት አባላት የብሄር ፓርቲዎችን ከማስቀረት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ ሆነዉ እንዲሰባሰብ ከማድረግ አንፃር አዋጁ ምን እንደያዘ ተጠይቋል።
የዲሞክራሲ ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እዉነቱ አለነ ይህንን አስመልክቶ ይህንን በፓርቲዎች ፍላጎት እንጂ በአዋጅ ይህንን ማድረግ የማይቻል እንደሆነ ተናግረዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1394/2017 አድርጎ በሁለት ተቃውሞ፤ በአራት ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አፅድቋል፡፡
ቁምነገር አየለ
ሐምሌ 10 ቀን 2017 ዓ.ም
