የኢራኑ ፕሬዝዳንት ከአልጀዚራ ጋር በነበራቸው ቆይታ ቴህራን የዩራኒየም ማበልፀግ ፕሮግራሟን እንደምትቀጥል አስታውቀዋል፡፡
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ሀገራቸው እስራኤል ለምትከፍትባት ማንኛውም ጦርነት ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል፡፡
በሀገራቱ መካከል በተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ብዙም ተስፋ እንደሌላቸው በመግለጽ፤ቴህራን ለሰላማዊ ዓላማ የጀመረችውን የኒውክሌር ፕሮግራም ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡
ይህ አስተያየት የመጣው ምዕራባውያን ሀገራት ከግጭቱ በኋላ ስለ ኢራን የኒውክሌር ምኞት መፍትሄ እንፈልጋለን ባሉበት ወቅት ሲሆን፤ በኒውክሌር ተቋማት ላይ የደረሰው ጥቃት ዋሽንግተን ከምትለው ያነሰ ጉዳት ማድረሱ እየተዘገበ ባለበት ወቅት ነው፡፡
ፔዜሽኪያን ለአልጀዚራ እንደተናገሩት ለማንኛውም አዲስ የእስራኤል ወታደራዊ እርምጃ ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ነን፤ የጦር ኃይላችንም በድጋሚ ወደ እስራኤል ለመግባት ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
ኢራን የ12 ቀኑን ጦርነት ያስቆመው የተኩስ አቁም ስምምነት ይዘልቃል ብላ እንደማታምንም ተናግረዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ‹‹በጣም ብሩህ ተስፋ የለንም››ያሉት ፔዜሽኪያን ለዚህ ነው ለማንኛውም ሊከሰት ለሚችል ሁኔታ እና ለማንኛውም ምላሽ ራሳችንን ያዘጋጀነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እስራኤል ጎድታናለች፤ እኛም ጎድተናታል፡፡ ከባድ ድብደባ አድርሳብናለች፤ እኛም በጥልቅ መትተናታል፤ ነገር ግን ኪሳራዋን እየደበቀች ነው ብለዋል፡፡
የእስራኤል ጥቃቶች ግንባር ቀደም ወታደራዊ ሰዎችን እና የኒውክሌር ሳይንቲስቶችን ከመግደል እና የኒውክሌር ተቋማትን ከማውደም ባለፈ የኢራንን የሥልጣን ተዋረድ ለማጥፋት ያለመ ነበር ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ይህን የማድረግ ዕቅዳቸዉ ከሽፏል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በሰኔ 24 ከተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት በፊት በኢራን አብዛኞቹ ሰላማዊ የሆኑ ከ9መቶ በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ፤ በእስራኤል በኩል ደግሞ ቢያንስ 28 ሰዎች ተገድለዋል ሲል አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
ሊዲያ ደሳለኝ
ሐምሌ 16/2017 ዓ.ም
