የቤተሰቤ ስም ችግር ፈጥሮብኝ አያውቅም
ሮማኖ ፍሎሪያኒ ሙሶሊኒ በጣሊያን ዝነኛ ከሆነ ቤተሰብ የተገኘ እግር ኳስ ተጫዋች ነው።
ፋሺስቱ አምባገነን መሪ ቤኒቶ ሙሶሊኒ ቅድመ አያቱ ናቸው።
የላዚዮው ተጫዋች በውሰት የሴሪ አውን ክለብ ክሬሞኔንሴ ከተቀላቀለ በኋላ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የእግር ኳስ ህይወቱ እንጂ የቤተሰቡ ስም ሊሆን እንደማይገባ ተናግሯል።
የ22 ዓመቱ ተጫዋች በዋናነት የሚጫወተው በቀኝ መስመር ተከላካይ ስፍራ ነው። በአማካይ ክፍል በቀኝ በኩል መጫወትም ይችላል።
ዘንድሮ ወደ ሴሪ አ ያደገውን ቡድን የተቀላቀለው ለአንድ የውድድር ዘመን በሚዘልቅ የውሰት ውል ቢሆንም ክሬሞኔንሴ በቆይታው በሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከተደሰተ በቋሚ ዝውውር ተጫዋቹን ማስፈረም እንደሚችል በስምምነቱ ላይ ተጠቅሷል።
ሐምሌ 17/2017 ዓ.ም
