ጉዳዩ ‹‹ብሄራዊ ህልውና›› በመሆኑ ሴቶች እስከ ስምንት ልጆች እንዲወልዱ ይበረታታሉም ተብሏል ።
ራሺያ ከዩኩሬን ጋር እያደረገችው ባለው ጦርነት ሳቢያ የህዝብ ብዛቷ በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ታች እያሽቆለቆለ መሆኑ ተገልጿል።
ይህ የተባለው በሀገሪቱ የስነ ህዝብ ብዛት አወቃቀር እና ጤና ላይ ያተኮረ ስብሰባ የሰራተኛ ሚኒስትሩ አንቶን ኮትያኮቭ ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ባደረጉበት ወቅት ነዉ፡፡
በውይይቱ ሚኒስትሩ በ2030 ራሺያ 11 ሚሊዮን አዲስ የስራ ሃይል ያስፈልጋታል ሲሉ አፅንኦት ሰጥተው ለፑቲን ተናግረዋል።
ኮትያኮቭ ይህ ቁጥር ያስፈለገው በተለያዩ ዘርፍ ላይ ያሉትን 10.1 ሚሊየን ለጡረታ የደረሱትን ለመተካት እና 8መቶ ሺህ የሚጠጉትን ደግሞ እንደ አዲስ ወደ ኢኮኖሚው ለማስገባት ነው ብለዋል።
እስከሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የውልደት መጠን ማሳደግ ካልተቻለ ሀገሪቱ ለከፍተኛ የሰራተኛ ሃይል ችግር ትጋለጣለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ሆኖም የወሊድ መጠንን ለመጨመር በሚደረገው ጥረት ዙሪያ የፑቲን የካቢኔ አባላት ትላልቅ ቤተሰቦች ላላቸው እንደ ገንዘብ እና የግብር እፎይታ ያሉ ማበረታቻዎችን ለመስጠት ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅት የራሺያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ፤የህዝብ ቁጥርን መጨመር ሀገራዊ ቀዳሚ ጉዳይ መሆኑን ገልፀው፣ ጉዳዩ ‹‹ብሄራዊ ህልውና›› በመሆኑ ሴቶች እስከ ሰምንት ልጆች እንዲወልዱ ይበረታታሉ ብለዋል።
እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2024 በሩሲያ ውስጥ ከ1999 ወዲህ የውልደት መጠን ወደ 1.22 ሚሊየን ዝቅ ብሏል የተባለ ሲሆን ፤ ሞት ደግሞ በ 3.3 በመቶ ጨምሮ ወደ 1.82 ሚሊዮን ማደጉን የባለስልጣኑ መረጃ ያሳያል።
የሩሲያ ህዝብ ባለፈው አመት 146 ሚሊዮን ገደማ ነበር ሲል የዘገበው ቢዝነስ ኢንሳይደር ነው።
ልዑል ወልዴ
ሐምሌ 21/2017 ዓ.ም
