አሜሪካ ፕሬዝዳንት ማዱሮን በቁጥጥር ሥር ላዋለልኝ የምሰጠውን ሽልማት በእጥፍ በማሳደግ 50 ሚሊየን ዶላር አድርሻለሁ አለች፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ፓም ቦንዲ፤ የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት በዓለም ላይ ካሉ ትልልቅ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች አንዱ ናቸው ብለዋል፡፡

አሜሪካ የቬንዙዌላውን ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የሚረዳ መረጃ ለሚያቀርብልኝ የ50 ሚሊየን ዶላር ሽልማት ሰጣለሁ ብላለች፡፡

ይህም በጥር ወር ከተወሰነው የ25 ሚሊየን ዶላር ሽልማት በእጥፍ ከፍ ያለ ነው፡፡

የቬንዙዌላው መሪ በዓለም ላይ ካሉ ቀዳሚ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች አንዱ እንደሆኑ የገለጸችዉ አሜሪካ፤ ከአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪ ቡድኖች ጋር በመተባበር ዩናይትድ ስቴትስን በኮኬይን ‹‹ለማጥለቅለቅ›› እየሰሩ ነዉ ስትል ከሳለች፡፡

የሽልማት ገንዘቡ ‹‹ታሪካዊ››ጭማሪ ማሳየቱን ያስታወቁት የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ፓም ቦንዲ፤ ማዱሮ ከቬንዙዌላ የወንጀል ቡድኖች እና በሜክሲኮ ከሚገኘው የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪ ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በዓለም ላይ ካሉ ትልልቅ የአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪዎች አንዱ ሲሆኑ፤ ለብሔራዊ ደህንነታችንም ስጋት ናቸው፡፡ ስለዚህ ሽልማቱን በእጥፍ በማሳደግ 50 ሚሊዮን ዶላር አድርገናል ብለዋል፡፡

በፕሬዝዳንት ትራምፕ አመራር ሥር ማዱሮ ከፍትህ አያመልጡም፤ለፈጸሙትም አሰቃቂ ወንጀል ተጠያቂ ይሆናሉ ያሉት ቦንዲ፤ህብረተሰቡ ጥቆማ መስጠት የሚችልበትን የስልክ መስመር ይፋ አድርገዋል፡፡

በተጨማሪም የዩናይትድ ስቴትስ የፍትህ መምሪያ እስካሁን ከማዱሮ ጋር ግንኙነት ያላቸው ከ7 መቶ ሚሊየን ዶላር በላይ የሚገመቱ ንብረቶች መያዙን ገልጸዋል፡፡

ሁለት የግል አውሮፕላኖች፣ ዘጠኝ ተሽከርካሪዎች እንደሚገኙበት እና በቶን የሚቆጠር የተያዘ ኮኬይን በቀጥታ ከፕሬዝዳንቱ ጋር ግንኙነት እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የቬንዙዌላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢቫን ጊል በበኩላቸው፤ የቦንዲን ማስታወቂያ እስከዛሬ ከታዩት ሁሉ ‹‹እጅግ አስቂኝ›› ሲሉ ገልጸው፤ በዩናይትድ ስቴትስ ከተፈጠረዉ የጄፍሪ ኤፕስታይን ውዝግብ ትኩረትን ለማስቀየር የተነደፈ ነው ብለዋል፡፡

ማዱሮ በ2020 የመጀመሪያው የትራምፕ ፕሬዝዳንታዊ ዘመን ከበርካታ የቅርብ አጋሮቻቸው ጋር በዩናይትድ ስቴትስ ፌዴራል ፍርድ ቤት በፌዴራል የአደንዛዥ ዕፅ ክሶች ተከሰው ነበር፡፡

በወቅቱ አሜሪካ ለእስራቸው የ15 ሚሊየን ዶላር ሽልማት አቅርባ ነበር፡፡

ይህ ገንዘብ በኋላ በባይደን አስተዳደር ወደ 25 ሚሊየን ዶላር ከፍ ብሏል፤ ይህም ዩናይትድ ስቴትስ ከመስከረም 11 ጥቃት በኋላ ኦሳማ ቢን ላደንን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ካቀረበችው የገንዘብ መጠን ጋር ተመሳሳይ ነው ሲል የዘገበዉ አልጀዚራ ነዉ፡፡

እስከዳር ግርማ

ነሐሴ 2/2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *