የሰላምን አማራጭ ባለመቀበል ችግር ለመፍጠር በሚነሡ ኃይሎች ላይ በተጠናከረ መንገድ ሕግ ለማስከበር እሰራለሁ ሲል መንግስት ገለፀ

የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት ከሐምሌ 30 -ነሐሴ 02 ቀን 2017 ዓ.ም ባደረገዉ መደበኛ ስብሰባ በዓለማዊ፣ አህጉራዊ፣ ቀጣናዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በዝርዝር መወያየቱን በመግለጫዉ ጠቅሷል።

ምክር ቤቱ በመግለጫዉ የሰሜኑን ጦርነት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መቋጨቱን አስታዉሶ። ጦርነቱን የተራዘመ ለማድረግ ሲፈልጉ የነበሩ አካላት ሌሎች ስልቶችን ወደ መሞከር ገብተዋል ሲል ገልፆል።

እነዚህ አካላት በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኞችን በመጠቀም የመንግሥትን ኃይልና የሕዝብን አንድነት ለመከፋፈል ጥረት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል ሲል መግለጫዉ አክሏል።

የፓርቲው ምክር ቤት ሲወያይባቸዉ በቆየባቸዉ ጉዳዩች ሀገሪቷን ከመንገዷ ለማስቀረት እየተደረጉ ነዉ ያላቸዉን ስልቶች መገምገሙን በመግለጫዉ ጠቅሷል።

ለግድያ የሚፈላለጉ ኃይሎችን በጥቅም ማስተሣሠር፤ በመልካም አስተዳደር ችግር የተነሣ የሚፈጠሩ የሕዝብ ቅሬታዎችን ለዐመጽ መጠቀም ናቸዉ ብሏል።

እንዲሁም በውጭ ምንዛሬ እና በሸቀጦች በኩል የኢኮኖሚ አሻጥርን መሥራት ናቸው ሲል አንስቷል።

መግለጫዉ አያይዞ ግጭትን ሊያስቀሩ የሚችሉ ሰላማዊ አማራጮችን በሁሉም አቅጣጫ ለመሞከርና በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ለሚወስኑ ታጣቂዎች አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ይሰራል ብሏል።

የሰላምን አማራጭ ባለመቀበል በሕዝብና በሀገር ንብረት ላይ ችግር ለመፍጠር በሚነሡ ኃይሎች ላይ በተጠናከረ መንገድ ሕግ ለማስከበር እንደሚሰራ ገልፆል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በብሔራዊ አጀንዳዎች ላይ ተጨባጭ ለዉጥ ማምጣቱን ገልፆል በመግለጫው።

በዓባይ ላይ ተገቢውንና ሕጋዊውን ተግባር በማከናወን በቀጣናው ጂኦስትራቴጂያዊ ቁመና መለወጥ እንዲሁም የባሕር በር የማግኘት ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብታችንን ዓለም አቀፍ አጀንዳ ማድረጉን አሳዉቋል።

ምክር ቤቱ በዲፕሎማሲው መስክ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች በሁሉም መንገድ ለማስከበር፤ ከመግባባት ላይ መድረሱን ካወጣዉ መግለጫ ተመልክተናል።

በተጨማሪ መጪው ሰባተኛ ሀገራዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ሕጋዊ፣ እና የሕዝቡ ምልዐተ ተሳትፎ የሚንጸባረቅበት እንዲሆን ተሳታፊ ይሆናል በማለት ምክር ቤቱ ገልፆል።

ነሐሴ 2/2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *