ከ16 ሺህ በላይ ወታደሮች እና ከ1መቶሺህ በላይ ከፊል ወታደራዊ ሰራተኞች ከስፍራዉ የመልቀቅ ስራ እንዲያግዙ ተደርጓል።
ባለሥልጣናቱ ለአውሎ ንፋስ ካጂኪ ምላሽ ለመስጠት ሲዘጋጁ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቬትናም የባህር ዳርቻ እንዲወጡ ታዘዋል፤ የአየር ማረፊያዎች እና ትምህርት ቤቶችም ተዘግተዋል።
መንግስት ባወጣው መግለጫ ይህ እጅግ በጣም አደገኛ እና በፍጥነት የሚንቀሳቀስ ማዕበል ነው፤ በማለት ካጂኪ ከባድ ዝናብ፣ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት እንደሚያመጣ አስጠንቅቋል።
በሰአት እስከ 1መቶ66 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ንፋስ ያለው አውሎ ንፋስ ሰኞ ከሰአት በኋላ መሬት እንደሚነካ የአገሪቱ የአየር ሁኔታ ኤጀንሲ ገልጿል።
በሁለት ግዛቶች የሚገኙ ሁለት አውሮፕላን ማረፊያዎች መዘጋታቸውን የቬትናም ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን አስታውቋል።
የቬትናም አየር መንገድ ሰኞ ወደ አካባቢው የሚደረጉ በደርዘን የሚቆጠሩ በረራዎችን ሰርዟል።
ቬትናም ብዙ ጊዜ ገዳይ ለሆኑ እና አደገኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ እና የመሬት መንሸራተት ለሚያስከትሉ አውሎ ነፋሶች የተጋለጠች ናት።
በአገሪቱ እርሻ ሚኒስቴር መረጃ መሠረት፤ በ2025 የመጀመሪያዎቹ ሰባት ወራት ውስጥ ከ1መቶ በላይ ሰዎች በተፈጥሮ አደጋዎች ሞተዋል ወይም ጠፍተዋል።
ባለፈው ዓመት አውሎ ንፋስ ያጊ ወደ 3መቶ የሚጠጉ ሰዎችን ገድሎ፤በግምት 3.3 ቢሊየን ዶላር የሚገመት የንብረት ውድመት አስከትሏል ሲል ያስታወሰዉ አልጀዚራ ነዉ።
እስከዳር ግርማ
ነሐሴ 19/2017 ዓ.ም
