እስራኤል በኳታር መዲና ዶሃ በፈጸመችው ጥቃት የሐማስ ተደራዳሪ ቡድን መትረፉን ቡድኑ አስታወቀ።
ሐማስ ባወጣው መግለጫ “ጠላት የተዳራዳሪ ልዑካችንን የመግደል ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል ብሏል።
መግለጫው አክሎም ጥቃቱ “ኔታንያሁ እና መንግሥታቸው ምንም አይነት ስምምነት ላይ መድረስ እንደማይፈልጉ ያረጋገጠ ነው” ብሏል።
እስራኤል ማክሰኞ፣ ጳጉሜ 4/ 2017 በዶሃ በፈጸመችው ጥቃት ስድስት ግለሰቦች መገደላቸውንም መግለጫው አክሏል።
“የአሜሪካ አስተዳደር በህዝባችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ወረራ እና ጥቃቶች ቀጣይነት ባለው መልኩ በመደገፍ ለዚህ ለተፈጸመው ጥቃት በጋራ ተጠያቂ ነው” ብሏል ሐማስ።
በሌላ ዜና የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ ሰፊ የምድር ጥቃት ላይ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ መላው የጋዛ ከተማ ነዋሪዎች አካባቢውን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ አስጠንቅቃለች፡፡
የጦሩ የአረብኛ ቋንቋ ቃል አቀባይ በጋዛ ትልቁ ከተማ የሚኖሩ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ አዝዘዋል።
ቃል አባዩ “በከተማዋ ውስጥ መቅረት በጣም አደገኛ ነው።” ብለዋል።
ሰኞ ዕለት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በቅርብ ቀናት በጋዛ ትላልቅ ሕንጻዎችን ያወደመው የአየር ጥቃት “የዋናው ጥቃት እና ከፍተኛ ዘመቻ መጀመሪያ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘመቻው የሐማስ የመጨረሻ ጠንካራ ይዞታን መቆጣጠር እንደሆነም ገልጸዋል።
ሐማስ በበኩሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ሰዎች በግዳጅ እንዲፈናቀሉ የሚያደርግ ወንጀል ነው ብሏል።
እስራኤል የጋዛ ከተማን የመውረር እቅዷም ዓለም አቀፍ ትችቶችንም አስከትሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ረሃብ እንደተከሰተ በታወጀበት አካባቢ የሚፈፀመው ጥቃት መባባስ ሰላማዊ ሰዎችን ወደ ባሰ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል ብሏል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል በጋዛ ከተማ በበተናቸው በራሪ ወረቀቶች እና በአረብኛ ቋንቋ ቃል አቀባዩ ኮሎኔል አቪቻይ አድሬ በማኅበራዊ ሚዲያ በተጋራው መልዕክት ላይ ግልጽ መልዕክት አስተላልፏል።
ጳጉሜ 5/2017 ዓ.ም
