የአፍላ ወጣቶች የእርግዝና ቁጥር እየጨመረ ነው ተባለ፡፡

በሀገሪቷ ላይ የሚስተዋለው አለመረጋጋት እና የጎጂ ባህል ድርጊቶች መቀጠል የአፍላ ወጣቶች እርግዝናን ቁጥር እንዲጨምር አድርጎታል ተባለ።

ዛሬ መስከረም 29/2018 አ.ም የጤና ሚኒስተር ከአምሊን የፌስቱላ ሆስፒታል እና ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በመሆን ሀገር አቀፍ የአፍላ ወጣቶች ቀንን አክብሯል።

በዝግጅቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስተር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ በኢትዮጵያ በርካታ ሴቶች ከ18 አመት በታች እንደሚዳሩ እና 13% የሀገሪቷ አፍላ ወጣቶች ደግሞ ላልተፈለገ እርግዝና እንደሚጋለጡ አስረድተዋል።

መስሪያ ቤታቸው ባለፉት 6 አመታት ለወጣቶች ልዩ ትኩረት ሰቶ እየሰራ እንደሚገኝ የጠቀሱት ሚኒስትር ደኤታው ከጎጂ ድርጊቶች ነፃ የሆኑ አካባቢዎችን በመፍጠር እንዲሁም ለወጣቶች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ፊስቱላን እና ያለ እድሜ የሚከሰት እርግዝናን መከላከል ተገቢ ነው ብለዋል።

ሚንስትሩ ”በትውልድ ላይ የሚሰራ ስራ ሁሌም ትርፍ እንጂ ኪሳራ የለውም” ያሉ ሲሆን ወጣቶችን ለማብቃት እና ለመጠበቅ ጤና ሚንስተር መዋቅር ዘርግቶ እና ስትራቴጂ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል።

በተጨማሪም በሀገሪቷ ላይ የሚስተዋለው አለመረጋጋት እና የጎጂ ባህል ድርጊት የአፍላ ወጣትነት እርግዝና ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት እየሆነ ይገኛል በማለት በጤና ሚኔስቴር የእናቶች ህፃናት እና አፍላ ወጣቶች ጤና መሪ አስፈፃሚ የሆኑት ዶ/ር ማርያማዊት አስፋው ተናግረዋል።

ሴቶች በመደፈር ያለ አቻ ጋብቻ እና በጠለፋ ምክንያት ለፊስቱላ እንደሚጋለጡ ዶ/ር ማርያማዊት ያስረዱ ሲሆን መስሪያ ቤታቸው ከተለያዩ ተቋማት ጋር ተባብሮ የአፍላ ህፃናት እርግዝናን ወደ 10% መቀነስ እንደቻለ በማንሳት ይህ አሀዝም ቢሆን በጣም ብዙ እናዳልሆነ እና መቀነስ የሚገባው ነው ብለዋል።

በጤና ሚኒስተር የአፍላ ወጣቶች እና ወጣቶች ጤና ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ዶ/ር ገመቺስ አቢ በበኩላቸው የአፍላ ወጣቶች እርግዝናን ለመቀነስ ሁሉም አካል ሊረባረብ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

የዘንድሮው ሀገር አቀፍ የአፍላ ወጣቶች ቀን ”አንድነት ለተግባራዊ እርምጃ የአፍላ ወጣትነት እርግዝናን ለማስቆም እንተባበር!” በሚል መሪ ቃል ለ ስድስተኛ ጊዜ ተከብሮ ውሏል።

ሀና ሰይፉ

መስከረም 29/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *