በ33 ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ሆስፒታሎች የጡት ካንሰር የመድኃኒት ሕክምና እንደሚሠጥም ተገልጿል፡፡
በየዓመቱ ወደ 16 ሺህ አዳዲስ የጡት ካንሰር ህሙማን ሲመዘገቡ፤ ከዚህ ዉስጥ 9ሺህ ያህሉ ህይወታቸዉን ያጣሉ ተብሏል፡፡
በጤና ሚኒስቴር የካንሰር መከላከልና መቆጣጠር አማካሪ ዶክተር ኩኑዝ አብዳላ ለኢዜአ እንዳሉት፤ እንደ ሀገር የጡት ካንሰር በሥርጭት ሁኔታ እና በሞት ምጣኔው ከካንሰር ዓይነቶች ቀዳሚ ነው።
የሞት ምጣኔውን ከፍ የሚያደርገው እና ለዘርፉ ተግዳሮት ከሆኑ ሁኔታዎች አንዱ አብዛኞቹ የጡት ካንሰር ህሙማን ወደ ሕክምና ተቋም መምጣት ከነበረባቸው ጊዜ እጅግ ዘግይተው መምጣታቸው መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል።
ከ70 በመቶ የሚልቁት የጡት ካንሰር ህሙማን ወደ ሕክምና የሚመጡት ህመሙ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ዘግይተው ነው፤ ቀደም ብለው ህመሙ በመጀመሪያ ደረጃ ላይ እያለ ቢመጡ መዳን ይችሉ ነበር ብለዋል።
ለመዘግየታቸው በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከልም የግንዛቤ እጥረት መሆኑን አንስተዋል።
የግንዛቤ መፍጠሩ ዓላማም ወደ ጤና ተቋም ዘግይቶ መምጣትን በመቀልበስ፤ በጊዜ እንዲመጡ ማድረግ መሆኑን ነው ያስረዱት።
በዋናነት አሁን በጤና ተቋማት እየተሠራ ያለው የጡት ካንሰር ቅድመ ልየታ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም በሁሉም የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ተቋማት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ስልጠና ከተሰጣቸው 3መቶ50 በመጀመሪያ አሃድ ላይ የሚገኙ የጤና ተቋማት መካከል 2መቶ36 ያህሉ የጡት ካንሰር ቅድመ ልየታ ሥራ እየሠሩ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሟላ የጡት ካንሰር ሕክምና ማለትም የቀዶ ሕክምና፣ የመድኃኒት ሕክምና እንዲሁም የጨረር ሕክምና የሚሰጡ አምስት የሕክምና ተቋማት መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
የዘንድሮው የጡት ካንሰር ወር “የጡት ካንሰርን በጊዜ በመለየት ሕይወትን እንታደግ” በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም
