የጃፓን ፓርላማ ሳናኤ ታካቺን የሀገሪቱ የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ መርጧል፡፡
ይህም በሀገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው ተብሏል።
ገዥውን ሊበራል ዴሞክራቲክ ፓርቲን የሚመሩት ታካቺ 4መቶ65 መቀመጫዎች ባሉት የታችኛው ምክር ቤት 2መቶ37 ድምፅ በማግኘት፣ 1መቶ49 ድምፅ ያገኙትን የሕገ መንግሥት ዴሞክራቲክ ፓርቲ እጩ ዮሺሂኮ ኖዳን አሸንፈዋል።
የጃፓን 104ኛዋ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆንም በከፍተኛው ምክር ቤት ድጋፍ አግኝተዋል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሺገሩ ኢሺባ ከምርጫ ሽንፈት በኋላ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ነዉ እርሳቸዉ የተሾሙት፡፡
ታካቺ የሦስት አስርት ዓመታት የፓርላማ ልምድ ያላቸዉ አንጋፋ ፖለቲከኛ ሲሆኑ፤ ቀደም ሲል የኢኮኖሚ ደህንነት ሚኒስትር እና የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል፡፡
ጃፓን በአምስት ዓመታት ውስጥ አምስተኛውን የጠቅላይ ሚኒስትር ለውጥ ያየች ሲሆን፤ይህም ሀገሪቱ በተደጋጋሚ የአመራር ሽግግር እንደምታደርግ የሚያሳይ ነዉ፡፡
አዲሱ መንግስት ኢኮኖሚውን እንደገና ለማነቃቃት፣ የስነ ሕዝብ አወቃቀር ችግሮችን ለመፍታት እና ጃፓን በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ያላትን ሚና ለማጠናከር ትኩረት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
እስከዳር ግርማ
ጥቅምት 11/2018 ዓ.ም
