የታንዛኒያዋ ፕሬዝዳንት ለሴት ልጃቸዉ እና ምራታቸዉ የካቢኔ ሹመት መስጠታቸዉ ተሰማ

የታንዛኒያዋ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሃሰን ሴት ልጃቸውን እና ምራታቸዉን ቁልፍ የመንግስት የስራ ቦታዎች ላይ ሹመት ሰጥተዋል፡፡

ሳሚያ ትናንት ባደረጉት የቴሌቪዥን ንግግር 27 ሚኒስትሮችን እና 29 ምክትል ሚኒስትሮችን ይፋ አድርገዋል፡፡

ልጃቸው ዋኑ ሃፊድ አሜር የትምህርት ሚኒስቴር ምክትል ሆነው የሚያገለግሉ ሲሆን፤ ባለቤታቸው መሀመድ ምቼንገርዋ ደግሞ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከነበረው ካቢኔ ሰባት ከፍተኛ ባለስልጣናት በሹመት ማሻሻያው ተተክተዋል።

የ43 ዓመቷ ልጃቸዉ በዛንዚባር የማኩንዱቺ የምርጫ ክልልን የሚወክሉ ሲሆን፤ የ46 ዓመቱ ባለቤታቸዉ ደግሞ በፕዋኒ ክልል የሩፊጂ የምርጫ ክልል ህግ አውጪ ናቸው።

የገንዘብ ሚኒስትሩ ካሚስ ሙሳ ኦማር ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑትን ምዊጉሉ ንኬምባን ተክተዋል።

አዲሱ ካቢኔ ዛሬ ይፋ የሚደረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የሳሚያ ሹመቶች በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ዘመዶቻቸውን ወይም አጋሮቻቸውን በመንግስት የስራ ቦታዎች ላይ የማስቀመጥ አዝማሚያን ያንፀባርቃል ተብሏል።

በተመሳሳይ በኡጋንዳ የፕሬዝዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ በርካታ የቤተሰብ አባላት በዋና ዋና የስራ ቦታዎች ላይ ይገኛሉ፡፡

ቀዳማዊት እመቤት ጃኔት ሙሴቬኒ የትምህርት ሚኒስትር ሲሆኑ፤ ልጃቸው ጄኔራል ሙሁዚ ካይኔሩጋባ ደግሞ የመከላከያ ሰራዊት አዛዥ ናቸው።

የሩዋንዳዉ ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ በቅርቡ ሴት ልጃቸውን አንጌ ኢንጋቢሬ ካጋሜን ለፖለቲካዊ ቦታ እያዘጋጁ ነው የሚለውን ትችት አስተባብለዉ እሷም ልዩ መብት እንደሌላት አጽንኦት ሰጥተዋል።

የፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ልጆች በሩዋንዳ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ ያገለግላሉ ሲል የዘገበዉ አፍሪካ ኒዉስ ነዉ።

ሀና ሰይፉ

ህዳር 09/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *