የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወርቁ የ2018 የበጀት ዓመት ምዝገባን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፣ አገልግሎቱ በመንግሥት ድጎማ አማካኝነት ለሚሊዮኖች ድጋፍ መስጠቱን አስታወቁ።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፣ አገልግሎቱ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት፣ በአጠቃላይ ከ4.3 ሚሊዮን በላይ መክፈል አቅም የሌላቸውን እማወራዎችና አባወራዎች በጤና መድህን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።
ይህ ትልቅ ስኬት ሲሆን፣ መንግሥት ለዜጎቹ የጤና ጥበቃ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
አገልግሎቱ በአጠቃላይ ከ63 ሚሊየን በላይ ዜጎችን የጤና መድን ሽፋን ስር ማድረስ ችሏል፤ ይህም 13.68 ሚሊዮን የሚሆኑ እማወራዎችንና አባወራዎችን ያካተተ ነው።
የዚህን ያህል ቁጥር ያለው አቅም የሌለው ዜጋ ተጠቃሚ ለማድረግ፣ ከመዋጮ ስብስቡ ውስጥ ከ7 ቢሊየን ብር በላይ የሚሆነው በመንግሥት የተደጎመ ገንዘብ መሆኑ ተገልጿል።
አገልግሎቱ እስካሁን እስካሁን በአጠቃላይ ከ19 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን አስታውቋል።
አቶ ተስፋዬ ወርቁ በመግለጫቸው፣ የጤና መድን አገልግሎቱ 1195 ወረዳዎችን ተደራሽ ማድረጉን ጠቁመዋል። ከእነዚህ ውስጥ 737 ወረዳዎች ገቢን መሠረት ያደረገ የመዋጮ ሥርዓትን ተግባራዊ እያደረጉ ነው።
ዋና ዳይሬክተሩ አገልግሎቱን ለማዘመን የፋይዳ መታወቂያ (Digital ID) አስፈላጊነት ላይ አጽንዖት ሰጥተዋል። በተጨማሪም የፋይናንስ ዘላቂነትን ለማረጋገጥ ሲባል፣ ቀደም ሲል የነበረው ኢ-ፍትሃዊ የገቢ ማሰባሰቢያ መንገድ ታርሞ ገቢን መሠረት ያደረገ የመዋጮ ወጪ እንዲሆን ማሻሻያ መደረጉን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት፣ የ2018 የበጀት ዓመት የአባላት ምዝገባ እና የመዋጮ ስብሰባ በአዲስ አበባ እና በሸገር ከተማ ከጥቅምት ወር ጀምሮ እስከ ህዳር መጨረሻ ድረስ እንደሚካሄድ አገልግሎቱ አስታውቋል
ለዓለም አሰፋ
ህዳር 16/2018 ዓ.ም
