ፍርድ ቤትም ለአሰሪዋ መወሰኑ ተሰምቷል
አንዲት ስፔናዊት ሴት ትሰራበት የነበረው ኩባንያ ብዙ ጊዜ ከስራ መግቢያ ሰአት በፊት ወደ ሥራ ትመጫለሽ ብሎ ስላባረራት ጉዳዩ በህግ ይታይልኝ ስትል ወደ ፍርድ ቤት ሄዳለች፡፡
ለሥራ ዘግይቶ መምጣት ከሥራ ለመባረር እንደ ምክንያት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ጉዳይ ቢሆንም፤በአንዳንድ አሰሪዎች ዘንድ ደግሞ ቀደም ብሎ መድረስም እንደ ከባድ ችግር ሊቆጠር ይችላል።
አንዲት ስፔናዊት ሴት ቶሎ ቶሎ ወደ ስራ እየመጣች እንደሆነ የሚገልጹ ማስጠንቀቂያዎችን ደጋግማ ችላ ብላ በማለፏ ምክንያት ራሷን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አግኝታዋለች፡፡
በአሊካንቴ በሚገኘው የዴሊቨሪ ድርጅት ውስጥ የምትሰራው ወጣቷ ምንም እንኳን ውሏ ከጠዋቱ 1፡30 ላይ ስራ መጀመር እንዳለባት የሚደነግግ ቢሆንም ከማለዳዉ 12፡45 እስከ ጠዋት 1ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ቦታዋ የመድረስ ልማድ ነበራት፣ይህም ማለት የስራ ፈረቃዋን የምትጀምረው ከስራ ባልደረቦቿ ቀደም ብላ ነበር፡፡
ታዲያ የወጣቷ ቀደም ብሎ ስራ መጀመር ስራ አስኪያጇን አላስደሰተም።
በዚሁ ልማዷ ምክንያት በ2023 ለመጀመሪያ ጊዜ ወቀሳ ቀርቦባት ነበር ፤ ነገር ግን በአስተዳደሩ የሚደርስባትን ቀጠን ያሉ ዛቻዎችን ችላ በማለት ቀድማ ወደ ስራ መድረሷን ቀጠለች።
ታዲያ በዚህ አመት መጀመሪያ ላይ አለቃዋ ‹‹በከባድ የስነ-ምግባር ጉድለት›› ሊያባርራት ወሰነ፡፡
ቀደም ብሎ ስራ ቦታ በመድረስ እና ምንም እንኳን ቀድማ ብትመጣም ለድርጅቱ ምንም አይነት አስተዋጽኦ እንደማታበረክት በመግለጽ ከስራ አሰናብቷታል፡፡
ነገር ግን ሰራተኛዋ ነገሮችን በዚህ መንገድ አላየችም በመሆኑም ውሳኔውን ወደ አሊካንት ማህበራዊ ፍርድ ቤት ወስዳ ተቃውማለች፡፡
ፍርድ ቤቱ ከአሰሪዋ ጎን በመቆም የአስተዳደር ማስጠንቀቂያዎችን በተደጋጋሚ ችላ በማለቷ ሁኔታው በሠራተኛ እና በአሠሪ ግንኙነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል ሲል ሁኔታውን አብራርቷል፡፡
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ “የሰራተኛዋ ባህሪ በታማኝነት ግንኙነት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል፤ ይህም በከፍተኛ ሁኔታ ድርጅቱን ይጎዳል፤ ድርጅቱ ለሰራተኛዋ በቂ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡ ነገር ግን ይህ ማስጠንቀቂያ በሰራተኛዋ በቂ ትኩረት አልተሰጠውም ብሏል፡፡
‹‹እምነት በመጣስ እና አለመታዘዝ›› በሚሉ ሁኔታዎች ሰራተኛዋ ጥፋተኛ ተብላ የስራ ግንኙነቱ መቋረጡ ተገቢ ነው በማለት ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡
ሀና ሰይፉ
ህዳር 30/2018 ዓ.ም
