ይህ የተገለፀው የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የሚችል የአረንጓዴ የሥራ እድሎች ላይ ያተኮረ ጉባኤ እና አውደ-ርእይ በአዲስ አለምአቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው።
በአካባቢ ጥበቃ ላይ ያተኮሩ የሥራ ዕድሎች ለሀገሪቱ ዘላቂ ልማት ያላቸውን ሚና ማጉላትና ህብረተሰቡ በዚህ ዘርፍ ላይ ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ የመድረኩ አላማ ነው።
በጉባዔዉ መክፈቻ ላይ የተገኙት በስራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴታ አቶ ሰለሞን ሶካ፤ “የአረንጓዴ የሥራ ዕድሎች፤ ለብሩህ ተስፋ” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው መድረክና ባዛር ከሀገሪቱ እቅድ ጋር የሚጣጣም ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ ከአከባቢ ጥበቃ ባሻገር የዚህ ጉባኤ መዘጋጀት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወጣቶችና ሴቶች በዚህ ዘርፍ እንዴት ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ማሳየትና የስራ እድሎችን ለማመቻቸት ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል።
የአካባቢን ደህንነት እየጠበቁ ገቢ ማስገኘት የሚችሉ አዳዲስ የቢዝነስና የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ለአደባባይ ማብቃት ያስችላል ሲሉም ሚንስትር ዴኤታው አቶ ሰሎሞን ሶካ አስረድተዋል።
የኤስ .ኤን.ቪ ፕሮግራም ዳይሬክተር የትናየት ግርማ በበኩላቸው ፤የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ኢኮኖሚ ለመገንባት፣ የአረንጓዴ የሥራ ዘርፎች ወሳኝ ሚና አላቸው ብለዋል።
ይህ ፕሮግራም ኢትዮጵያ ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር ትልቅ ግብአት መሆኑንም ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
በተለምዶ ከሚታወቁት የስራ መስኮች ውጪ፤ በቆሻሻ መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል፣ በታዳሽ ኃይልና በከተማ ግብርና ዘርፎች ሰፊ የስራ እድል መፍጠር ያስችላል ሲሉም ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።
በተጨማሪም እንደ ስዊድንና ኔዘርላንድ ኤምባሲዎች ያሉ ዓለም አቀፍ አካላት መሳተፋቸው፤ ለዘርፉ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና የቴክኒክ ድጋፍን ለመሳብ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
ይህ ጉባኤ በLIWAY ፕሮግራም አማካኝነት የስዊድን እና ኔዘርላንድ ኤምባሲዎች በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን፣ በSNV እና MercyCorps ይተገበራል ተብሏል ።
የኢትዮጵያን የወደፊት የኢኮኖሚ አቅጣጫ የሚጠቁም፣ ለወጣቶች የስራ ተስፋን የሚፈነጥቅ እና ዓለም አቀፍ ትብብርን ያሳያል የተባለው ጉባኤ እና አውደርዕይ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት ክፍት ይሆናል ተብሏል።
ልዑል ወልዴ
ህዳር 30/2018 ዓ.ም
