የአሜሪካ ጦር በፓሲፊክ ውቅያኖስ ውስጥ ህገወጥ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ላይ ተሰማርተዋል ብሎ በወነጀላቸው ሶስት ጀልባዎች ላይ በወሰደው የአየር ጥቃት ስምንት ሰዎችን መግደሉን አስታዉቋል።
የአሜሪካ ደቡባዊ ዕዝ የጥቃቱን ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያጋራ ሲሆን፤ ጀልባዎቹ በታወቁ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር መስመሮች ላይ እየተጓዙ እና በዝውውሩ ተግባር ላይ ተሰማርተው እንደነበር ገልጿል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቀጣናው አደንዛዥ ዕፅ ያዘዋውራሉ ባሏቸው ቡድኖች ላይ የጀመሩት ዘመቻ ተጠናክሮ ሲቀጥል፤ በቅርብ ወራት በፓሲፊክ እና በካሪቢያን ከ20 በላይ ጀልባዎች ኢላማ ተደርገው ቢያንስ 90 ሰዎች ተገድለዋል።
አንዳንድ ባለሙያዎች እነዚህ ጥቃቶች የትጥቅ ግጭትን የሚቆጣጠሩ ዓለም አቀፍ ህጎችን ሊጥሱ እንደሚችሉ ይገልጻሉ።
የትራምፕ አስተዳደር ቬንዙዌላን አደንዛዥ ዕፅ ወደ አሜሪካ ታስገባለች ሲል የከሰሰ ሲሆን፤በቅርብ ወራት ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን ለማግለል የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሯል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች እና የዓለማችን ትልቁ የአውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ የሆነው ዩኤስኤስ ጄራልድ ፎርድ ቬንዙዌላን ማጥቃት በሚያስችል ርቀት ላይ እንዲሰፍር ተደርጓል ሲል የዘገበዉ ቢቢሲ ነዉ።
ቃልኪዳን ተክሉ
ታህሳስ 07/2018 ዓ.ም
