በቤኒን በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ከተደረገው የከሸፈ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጋር በተያያዘ አብዛኛዎቹ ወታደሮች የሆኑ 30 ሰዎች መታሰራቸውን የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤ ኤፍ ፒ ዘግቧል።
ወታደሮቹ የመንግስት ቴሌቪዥን ጣቢያን በመቆጣጠር መንግስት መፍረሱን አውጀው ነበር።
ነገር ግን ይህ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራቸው ለመንግስት ታማኝ በሆኑ የሠራዊቱ አባላት፣ በአየር ድብደባ፣ እንዲሁም ከናይጄሪያ እና ከሌሎች የምዕራብ አፍሪካ አጋሮች በተገኘ ወታደራዊ ድጋፍ ሊከሸፍ ችሏል።
ፈረንሳይም የሎጂስቲክስ ድጋፍ አድርጋለች።
ኤ ኤፍ ፒ እንደዘገበው ተከሳሾቹ ማክሰኞ ዕለት የቅድመ-ፍርድ ቤት ውሎ ከተደረገ በኋላ ወደ እስር ቤት ተልከዋል።
በግለሰቦቹ ላይም የሀገር ክህደት፣ የግድያ እና የሀገርን ደህንነት አደጋ ላይ የመጣል ክስ ተመስርቶባቸዋል።
መፈንቅለ መንግስቱን መርተዋል የተባሉት ሌተናል ኮሎኔል ፓስካል ቲግሪ አሁንም በሽሽት ላይ ናቸው። የቤኒን ባለስልጣናት ግለሰቡ ወደ ቶጎ ዋና ከተማ ሎሜ መሸሻቸውን ይናገራሉ።
የቤኒን መንግስት ቶጎ እኚህን ግለሰብ እና ሌሎች የሸሹ ወታደሮችን አሳልፋ እንድትሰጥ ጠይቋል።
አማጺ ወታደሮቹ ፕሬዝዳንት ታሎን በሰሜን ቤኒን ያለውን የጸጥታ ሁኔታ በአግባቡ አልተቆጣጠሩም በሚል የከሰሱ ሲሆን፤ በጤና እና በሌሎች የህዝብ አገልግሎቶች ላይ የተደረገውን ቅነሳም ተችተዋል።
በተጨማሪም ፕሬዝዳንቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን አፍነዋል ሲሉ ከሰዋል።
እስከዳር ግርማ
ታህሳስ 08/2018 ዓ.ም
