’‘መሬት የመንግስት ነው’‘ የሚለውን በሕግ ማብራራት ቢቻልም ”የህዝብ ነው” ወይም ’‘የብሔር ብሔረሰቦች ነው‘’ የሚለው አገላለጽ ግን በሕግ ሊብራራ የማይችልና ተጨባጭ ያልሆነ ነው ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህሩ መለሰ ዳምጤ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
መለሰ ዳምጤ (ዶ/ር) ይህን የገለጹት ’ላንድ ፎር ላይፍ ኢትዮጵያ‘ ባዘጋጀውና በመሬት አስተዳደር ጉዳዮች ላይ በተደረገ የሚዲያ ተሳትፎ፣ የአቅም ግንባታ እና አውደ ጥናት ላይ በፕላቲኒየም ሆቴል በሰጡት ማብራሪያ ነው፡፡
‘‘መሬት የህዝብ ነው‘’ ወይም ’‘የብሔር ብሔረሰቦች ነው‘’ የሚለው አገላለጽ በሕግ እይታ ለማብራራት፣ ሕዝብ ወይም ብሔር ብሔረሰብ እንዴት ነው በመሬቱ ላይ የሚያዘው? እንዴት ነው የሚጠቀመው? መሬቱን እንዴት ነው የሚወስደው? የሚሉና ሌሎችም ዝርዝር ጉዳዮች ሲነሱ ምላሽ መስጠት አስቸጋሪ እንደሆነ ነው የሕግ መምህሩ ያስረዱት፡፡
የኢትዮጵያ መሬት ሙሉ በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን ”መሬት የመንግስት ነው’‘ የሚለውን በሕግ ማብራራት ቢያስፈልግ መሬትን እንደሚያስተዳድር፣ የሚሰጠውም ሆነ የሚወስደው መንግስት እንደሆነና ሌሎችም ተግባራት የሕግ መሰረት ያላቸው መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በመሆኑም ’‘መሬት የመንግስት ነው’‘ የሚለው ተጨባጭ የሕግ መነሻ እንዳለው፣ ‘‘መሬት የህዝብ ነው‘’ ወይም ’‘የብሔር ብሔረሰቦች ነው‘’ የሚለው አገላለጽ ግን አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሕግ ትርጉም እንደሌለው ነው የገለጹት፡፡
በኢትዮጵያ መሬት ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ይልቅ የፖለቲካ መጠቀሚያነቱ እንደሚጎላ አንስተው፣ ከፊውዳሊዝም ዘመን ጀምሮ የፖለቲካ መጠቀሚያ መሆኑ ደግሞ የህዝቡ ኑሮ የተሻለ እንዳይሆን ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
አውደ ጥናቱን ያዘጋጀው የላንድ ፎር ላይፍ ኢትዮጵያ ሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ፍቅሩ ታከለ በበኩላቸው ድርጅቱ መንግሥታዊ ያልሆነ እና ለትርፍ ያልተቋቋመ መሆኑን ገልጸው፣ በመሬት አስተዳደር እና ኃላፊነት የተሞላበት የግብርና ኢንቨስትመንቶች ላይ ያሉ ዉይይቶችን እንዲሁም ትብብሮችን ለማሣደግ የሚሰራ ቁርጠኛ ድርጅት ነው ብለዋል።
ህዝብን ያማከለ የመሬት አስተዳደርን ማስተዋወቅ እና ማበረታታት፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተለይም የማህበረሰብ ተወካዮች፣ አካታች እና ግልጽ የመሬት ፖሊሲዎችን ለማዳበር እና ተግባራዊ ለማድረግ አስተዋፅዖ የሚያደርጉበት መድረክ ለመፍጠር እንደሚሰራም ተናግረዋል።
አዲስአለም አበበ
ታህሳስ 08/2018 ዓ.ም
