በትግራይ ክልል 15 በሚሆኑ ወረዳዎች ላይ የጤና መድህን አገልግሎት መልሶ ለማስጀመር እየተሰራ ነዉ ተባለ

በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ ክልል ተቋርጦ የነበረው የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት በድጋሚ ሊጀምር ነው።

በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ ክልል ተቋርጦ የነበረውን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት በድጋሚ ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት አስታወቋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃም የአገልግሎቱ ሽፋን 84 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዳምጠው ጥላሁን እንደገለጹት፤ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው ጦርነት ምክንያት በትግራይ ክልል በ2010 እና 2012 ዓ.ም ተጀምሮ የነበረው የአገልግሎት ስርጭት ተቋርጦ መቆየቱን አስታዉሰዋል።

አሁን ላይ አገልግሎቱን መልሶ ለማስጀመር ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አቶ ዳምጠው እንዳሉት፥ በክልሉ አገልግሎቱን መልሶ ለማስጀመር ከ10 እስከ 15 በሚሆኑ ወረዳዎች ላይ እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተርም ጉዳዩን አስመልክቶ ለመምከር መቀሌ ሔደዉ እንደነበር አንስተዋል።

በቀጣይም በትግራይ ክልል ያሉ 93 ወረዳዎችን እንዲሁም በሶማሌ ክልል የሚጨመሩ 32 ወረዳዎችን ጨምሮ ሽፋን ለማሳደግ ታቅዷል።

በመጨረሻም የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አደረጃጀት በክልል፣ በዞንና በወረዳ ደረጃ ያለውን ክፍተት ለመፍታትና ወጥ የሆነ መዋቅር ለመዘርጋት አንድ አጥኚ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥናት እያደረገ መሆኑን ኃላፊው አንስተዋል።

ሊዲያ ደሳለኝ

ታህሳስ 08/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *