በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚያጋጥሟቸውን የፋይናንስ ተግዳሮቶች ለመቅረፍ ያለመ ከፍተኛ ደረጃ ያለው ሲምፖዚየም እና ኤግዚቢሽን ዛሬ በአዲስ አበባ ተከፍቷል።
ኤስ.ኤን.ቪ በተሰኘው ዓለም አቀፍ ድርጅት እና በሊዊ ፕሮግራም አማካኝነት በተዘጋጀው በዚህ መድረክ ላይ፤ የንግድ ባንኮች፣ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት፣ የፊንቴክ ኩባንያዎች እና የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የሲምፖዚየሙ ዋና ዓላማ በተለይም በሴቶችና በወጣቶች የሚመሩ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በቀላሉ የፋይናንስ አገልግሎት የሚያገኙበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠርና የዘርፉን ተዋናዮች እርስ በእርስ ማገናኘት መሆኑ ተገልጿል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የSNV የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ጁሊ ግርሃም፤ ኢንተርፕራይዞቹ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገትና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ የብድርና የፋይናንስ አቅርቦት ዋነኛ ማነቆ ሆኖባቸዋል ብለዋል።
ከውይይቱ ጎን ለጎን በተዘጋጀው የፋይናንስ ምርቶች ኤግዚቢሽን ላይ ባንኮች እና የፋይናንስ ተቋማት ለአነስተኛ ነጋዴዎች ያዘጋጇቸውን አዳዲስ የዲጂታል የብድር አይነቶችና አገልግሎቶች እያስተዋወቁ ይገኛሉ።
ይህ የአንድ ቀን ሲምፖዚየም በዘርፉ ያሉ የፖሊሲ ማነቆዎችን በመለየትና የጋራ መፍትሄዎችን በማመላከት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።”
ልኡል ወልዴ
ታህሳስ 08/2018 ዓ.ም
