ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በፍሎሪዳ ተገናኝተው መከሩ

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በፍሎሪዳ በሚገኘው የማር-አ-ላጎ መኖሪያ ተገናኝተው በወቅታዊ የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል። ይህ ስብሰባ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ስልታዊ አጋርነት ለማጠናከር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

እንደ ቤተ መንግስት ምንጮች ገለጻ፣ የሁለቱ መሪዎች ውይይት በዋናነት ያተኮረው በጋዛ ባለው ግጭት ታጋቾችን በማስለቀቅ ሂደት እና በክልሉ እየታየ ባለው የጸጥታ ስጋት ዙሪያ ነው።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በውይይቱ ወቅት እስራኤል ራሷን የመከላከል መብቷ የተጠበቀ መሆኑን በድጋሚ በማረጋገጥ በመካከለኛው ምስራቅ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው አሜሪካ ለእስራኤል ለምትሰጠው ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

መሪዎቹ በተለይም የአብርሃም ስምምነትን በማስፋት እስራኤል ከጎረቤት የዓረብ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ መክረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፖለቲካ ተንታኞች ይህንን ስብሰባ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ትልቅ ተፅእኖ ሊኖረው የሚችል ክስተት አድርገውታል።

በተለይም በኢራን የኒውክሌር መርሃ-ግብር እና በክልሉ በሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ቡድኖች ላይ የሚወሰደው አቋም ይበልጥ ጠንካራ ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን እየሰጡ ይገኛሉ።

የሁለቱ መሪዎች ስብሰባ መጠናቀቅን ተከትሎ በወጣው መግለጫ ሁለቱም ሀገራት በጸጥታ እና በደህንነት ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ቅንጅት ይበልጥ ለማሳደግ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተጠቁሟል።

ሱፊያን አህመድ

ታህሳስ 21/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *