በሶማሌ፣ በአፋር እና በጋምቤላ ክልሎች የበጀት እጥረት የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እንቅፋት መሆኑ ተገለፀ

በኢትዮጵያ የሴቶች የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ አሁንም ከ50 በመቶ በታች መሆኑም ተገልጿል።

በተለይም በሶማሌ፣ በአፋር እና በጋምቤላ ክልሎች ሴቶችን ለማብቃት የሚሰሩ ስራዎች በበጀት እጥረት ምክንያት ፈተና እንደገጠማቸው የክልሎቹ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊዎች ገልጸዋል።

በሶማሌ ክልል የሴቶች እና ህጻናት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ወይዘሮ ሀሊማ ሀሰን እንደገለጹት፣ በክልሉ የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ በተለይም እስከ 10ኛ ክፍል ባለው ደረጃ ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል።

ይሁን እንጂ ለዘርፉ የሚመደበው በጀት አነስተኛ መሆን፣ በዕቅድ ዝግጅት እና በክትትል ስራዎች ላይ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

በተመሳሳይ በአፋር ክልል የሚገኙ 6 ዞኖችና 45 ወረዳዎች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ለመስራት መቸገራቸውን የገለጹት የአካቶ ትግበራ ክትትል እና ቁጥጥር ዳይሬክተር አሚና ሙሳ ናቸው።

በበጀት እጥረት ምክንያት የሚፈጠር የትራንስፖርት ችግር ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች የሚኖረውን ማህበረሰብ ለማስተማር ትልቅ እንቅፋት መሆኑን ዳይሬክተሯ አብራርተዋል።

ማህበረሰቡን ለማወያየት የሚረዱ የሻይ ቡና ፕሮግራሞችን ለማዘጋጀት እንኳ ያለው በጀት እጅግ አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

የጋምቤላ ክልል የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አርያት ኡጁሉ በበኩላቸው፣ ቀደም ሲል ሴቶች በቤት ውስጥ ብቻ እንዲወሰኑ የሚያደርገው አመለካከት አሁን ላይ እየተቀየረ መሆኑን ገልጸዋል።

ሆኖም ግን የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበጀት እጥረት አሁንም ስራዎችን በጥራት ለመስራት አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው ተናግረዋል።

ለአለም አሰፋ

ጥር 05/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *