አንዲት ሴት ባሌ መላጣ መሆኑን ደብቆ አግብቶኛል ስትል ክስ መሰረተች

በህንድ ኖይዳ ግዛት ነዋሪ የሆነችው ላቪካ ጉፕታ፣ ከሁለት ዓመት በፊት ትዳር የመሰረተችው ባለቤቷ “መላጣ መሆኑን ደብቆኛል” በማለት በፖሊስ ጣቢያ ክስ መመስረቷ ተሰምቷል።

ላቪካ ጉፕታ በኖይዳ በሚገኘው ቢስራክ ፖሊስ ጣቢያ ባቀረበችው የክስ መዝገብ መሰረት፣ ባለቤቷ ሳንያም ጄን እሷን እና አራት የቤተሰቡ አባላት በማታለል ወንጀል ተጠያቂ እንዲሆን ጠይቃለች።

ላቪካ እንደገለጸችው እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 2024 ጋብቻው ከመፈጸሙ በፊት “ጥሩና ያማረ ፀጉር ያለው ሰው” እንደሆነ ተነግሯት የነበረ ቢሆንም፣ ከጋብቻ በኋላ ግን ባለቤቷ መላጣ መሆኑንና በዊግ (ሰው ሰራሽ ፀጉር) ይሸፍነው እንደነበር ደርሼበታለሁ ብላለች።

የሴቲቱ ክስ በፀጉር ጉዳይ ላይ ብቻ የተገደበ አይደለም። ላቪካ እንደገለጸችው ባለቤቷ በሌሎች በርካታ ጉዳዮች ላይም አታሏታል።

ባሏ የንግድ ዲግሪ እንዳለው ቢገለጽላትም፣ በትክክል ግን የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን ብቻ ያጠናቀቀ ሆኖ ተገኝቷል።

በተጨማሪም በዓመት 20,000 ዶላር ገቢ እንዳለው ቢነገራትም፣ ይህ መረጃ ግን ሀሰት መሆኑን አረጋግጫለሁም ብላለች።

በተጨማሪም ባለቤቷ ወደ ውጭ አገር በሄዱበት ወቅት ድብደባ እንደፈጸመባትና ከታይላንድ ወደ ህንድ ማሪዋና እንድታመጣለት ተጽዕኖ ሲያሳድርባት እንደነበርም በክሱ ላይ አካታለች።

የህንድ ቢስራክ ፖሊስ ጣቢያ ባለስልጣናት ጉዳዩን በማጣራት ላይ እንደሚገኙም ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።

ሀና ሰይፉ

ጥር 05/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *