ባንኩ ላለፈው አንድ ዓመት ሲተገብረው የቆየውን አጠቃላይ የሴቶችን አቅም የማጎልበት ፕሮግራም አፈጻጸም ዛሬ በፓናል ውይይት ገምግሟል።
የዳሸን ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ዳሽን ባንክ ከምስረታው ጀምሮ ላለፉት 30 ዓመታት የሴቶችን አቅም በማጎልበትና ወደፊት በማምጣት የተለያዩ ሴት አመራሮች አስተዋፅኦ ተጠቃሚ መሆን መቻሉን አስታውሰዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሴቶች በተለያዩ የአመራር እርከኖች በማገልገል ለባንኩ የወደፊት እርምጃ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡
ዳሸን ባንክ ይህን ለ30 ዓመታት የዳበረ ተሞክሮ ለማጠናከርና የሴቶችን አቅም ይበልጥ በማጎልበት ሴቶች ወደተለያዩ የአመራር እርከኖች ከፍ ማለት ይችሉ ዘንድ የተቀናጀ የሴቶች አቅም ግንባታ መርሃ ግብርን ከአንድ አመት በፊት አስጀምሮ የተለያዩ ስኬቶችን ከወዲሁ እያስመዘገበ ነው፡፡
በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ከ1መቶ40 በላይ የሚሆኑ ሴት የባንኩ ባልደረቦች በዚህ መርሃግብር የመሳተፍና በተለያዩ መንገዶች አቅማቸውን የማጎልበት እድል እንዳገኙ ተጠቁሟል፡፡
ሴቶች በዚህ መድረክ አማካኝነት የሚያገኟቸው የአመራር ክህሎትና አቅም ግንባታ ስልጠናዎች ለባንኩ ስኬት የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ስለሆነ ለወደፊትም ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመላክቷል፡፡
ዳሸን ባንክ ካሉት ከ11 ሺ በላይ ቋሚ ሰራተኞች ከ3ሺህ3መቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።
ሀና ሰይፉ
ጥር 14/2018 ዓ.ም
