በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የመንግስት ሰራተኞች፣ ለጡረታ ባለመብቶች እና ለቤተሰቦቻቸው የማህበራዊ ጤና መድህን ተጠቃሚነት መርሃ ግብር ዛሬ ጥር 14 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወርቁ፤ በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት፣ የጤና ባለሙያዎች ለህዝብ ጤና ሲሉ የሚከፍሉትን የላቀ መስዋዕትነት እና ያላቸውን ከፍተኛ ሚና መንግስት ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት፣ ሰራተኞቹ የጤና እክል ሲያጋጥማቸው ተገቢውን የህክምና ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል ተብሏል።
በአዲሱ የጤና አገልግሎት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1363/2017 መሰረትም፣ ለእነዚህ ሰራተኞች የሚከፈለው ሙሉ የአባልነት መዋጮ በመንግስት የሚሸፈን መሆኑ ተመላክቷል።
አገልግሎቱ በዘመናዊ የዲጂታል ስርዓት ተደራጅቶ የቀረበ ሲሆን፤ በዚህም 1መቶ81 ሺህ በቋሚነት ተቀጥረው የሚሰሩ የዘርፉ ሰራተኞች እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ በአጠቃላይ 4መቶ75 ሺህ ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተነግሯል።
የተጠቃሚዎች ምዝገባ ሂደት እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ተከናውኖ መጠናቀቁን እና ይህም ለስራው መጀመር ምቹ ሁኔታን መፍጠሩ ተጠቅሷል፡፡
በተጨማሪም አባላቱ ጥራት ያለው ህክምና ያለምንም እንግልት እንዲያገኙ ለማስቻል በመላ ሀገሪቱ ከሚገኙ 2 ሺህ8መቶ15 የጤና ተቋማት ጋር የውል ስምምነት መደረጉን ጣቢያችን ሰምቷል።
ይህም ተጠቃሚዎች በአቅራቢያቸው በሚገኙ ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች አስፈላጊውን ህክምና እንዲያገኙ የሚያስችላቸው መሆኑ ተገልጿል።
የጤና መድህን አገልግሎት በቀጣይም የአገልግሎት ጥራትን በማረጋገጥና ክፍተቶችን በመሙላት ስርዓቱን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰራ አስታውቋል።
ሐመረ ፍሬው
ጥር 14/2018 ዓ.ም
