ለማኝ መስሎ ሲለምን የነበረው ግለሰብ የበርካታ ቤቶች፣ ተሽከርካሪዎችና የንግድ ሥራዎች ባለቤት ሆኖ ተገኘ::

በሕንድ ማድያ ፕራዴሽ ግዛት በኢንዶር ከተማ ጎዳናዎች ላይ በሥጋ ደዌ በሽታ ተጠቅቶ ሲለምን የነበረ አንድ ግለሰብ፣ በርካታ ንብረቶች፣ ተሽከርካሪዎችና የንግድ ተቋማት ያሉት እውነተኛ “ባለጸጋ ለማኝ” ሆኖ ተገኝቷል።

የኢንዶር ከተማ አስተዳደር ከተማዋን ከለማኞች ነፃ ለማድረግ ባደረገው የተቀናጀ ጥረት፣ በሳራፋ ባዛር ውስጥ ለዓመታት ሲለምን የነበረን አንድ አካል ጉዳተኛ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር አውሏል።

ማንጊላል ተብሎ የሚጠራውና ዕድሜው 50 ዓመት የሆነው ይህ ግለሰብ፣ በእግሩ መጓዝ ስለማይችል ጎማ በተገጠመለት ትንሽ የእንጨት ሳህን ላይ ተቀምጦ ራሱን እየገፋ የሚንቀሳቀስ ሲሆን ጣቶቹን በሥጋ ደዌ በሽታ ምክንያት በማጣቱ፣ የሚያዩት መንገደኞች ሁሉ አዝነውለት ሳንቲም ይመጸውቱት ነበር።

ማንጊላል ሰዎችን ፈጽሞ አይለምንም፤ ይልቁንም መሬት መሬቱን እያየ በእንጨት ሳህኑ ላይ ዝም ብሎ ይቀመጣል። ይህ ሁኔታው ደግሞ ሰዎች ይበልጥ እንዲያዝኑለት ያደርጋቸዋል።

ይሁን እንጂ ድርጊቱ በዓለም ላይ ካሉ ጤነኛ ሰዎች በበለጠ እንዲበለጽግ ያደረገው በጥንቃቄ የታቀደ ስትራቴጂ ሆኖ ተገኝቷል።

ባለሥልጣናት ግለሰቡን ወስደው ገላውን ካጠቡትና ንጹህ ልብስ ካለበሱት በኋላ ስለ ሁኔታው ሲጠይቁት፣ እንደሚታየው ረዳት የሌለው ምስኪን እንዳልሆነ ተረድተዋል። ግለሰቡ በቀን በሺዎች የሚቆጠር ሩፒ ከመለመኑም በላይ፣ በሳራፋ ባዛር ውስጥ ለሚገኙ ነጋዴዎች በወለድ ገንዘብ ያበድር ነበር።

የተደረገው ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያሳየው ግለሰቡ የቤት አልባ ሳይሆን የሦስት ቤቶች ባለቤት ሲሆን ከእነዚህም መካከል ባለ ሦስት ፎቅ ሕንፃ፣ ሌላ ሁለተኛ ቤት እና በመንግሥት የበጎ አድራጎት ፕሮግራም የተሰጠው አንድ አፓርታማ ይገኙበታል።

በተጨማሪም ለሰዎች ያከራያቸው ሁለት ባጃጆች”እና በወር 12,000 ሩፒ (130 ዶላር) ደሞዝ የሚከፍለው አሽከርካሪ ያለው የመኪና ባለቤት መሆኑ ታውቋል።

ማንጊላል እራሱ እንደተናገረው፣ ከልመና የሚያገኘው ገቢ ለዕለት ጉርሻ ሳይሆን ለተለያዩ ኢንቨስትመንቶች መዋያ የሚሆን የገንዘብ ምንጭ ነው። ባለሥልጣናት አሁንም በስሙ የተመዘገበ የባንክ አካውንት መኖሩን እያጣሩ ሲሆን፣ በምርመራው ወቅት የቤተሰቡ አባላትም በልመና ሥራ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ተገልጿል።

በኢንዶር ከተማ ልመና በሕግ የተከለከለ መሆኑን ያወቀው ማንጊላል ሲከላከል “እኔ ወደዚያ እሄዳለሁ እንጂ አልለምንም፤ ሰዎች ራሳቸው ናቸው በኪሴ ውስጥ ገንዘብ የሚከቱት ወይም በእንጨት ሳህኑ ላይ ሳንቲም የሚጥሉልኝ” ሲል ተናግሯል።

ሐመረ ፍሬው

ጥር 19/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *