የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመጀመሪያ ጊዜ የደንበኞቹ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ2 ትሪሊዮን ብር በላይ መሻገሩን አስታውቋል ።
ባንኩ “የእርስዎ እርካታ፤ የባንካችን ስኬት” በሚል መሪ ቃል የደንበኞች አገልግሎት ሳምንትን በዛሬው ዕለት በይፋ ጀምሯል።
በአዲስ አበባ በተከናወነው የደንበኞች አገልግሎት ሳምንት የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ የታደሙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እያስመዘገበ ያለውን ውጤትና የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ጉዞ የተመለከቱ አሃዞችን ይፋ አድርገዋል።
ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን 2 ትሪሊዮን ብር ያለፈ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም ከ 45 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን እያገለገለ ይገኛል።
ይህም ባንኩ በሀገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ያለውን የ 50 በመቶ የገበያ ድርሻ አጠናክሮ እንዲቀጥል አስችሎታል ብለዋል።
መንግስት የባንኩን የሀብት ጥራትና ጥንካሬ ለመጠበቅ እስከ 900 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ቦንድ በማተም ድጋፍ ማድረጉን የገለጹት አቶ አህመድ ሽዴ፤ በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገው የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን መደረጉ ለባንኩ ውጤታማነት የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።
ከባንኩ ስኬት ባሻገር የሀገሪቱን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሁኔታ የዳሰሱት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ባለፈው በጀት ዓመት 9.2 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቧን አስታውሰው፣ በያዝነው ዓመት ደግሞ ይህ ዕድገት ወደ 10.2 በመቶ ከፍ ይላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዛሬው ዕለት የጀመረው የደንበኞች አገልግሎት ሳምንት፤ ደንበኞቹን ይበልጥ ለማቅረብና የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
ልኡል ወልዴ
ጥር 19/2018 ዓ.ም
